ሰንደቅ ዓላማ ከቀለማት ስብስብ በላይ የሕዝቦች ነፃነት፣ የሉዓላዊነት፣ የታሪካዊ ገድል እና የጋራ ማንነት ሕያው ምልክት ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ረጅም የነፃነት ታሪክ ላላት ሀገር ደግሞ የሰንደቅ ዓላማ ትርጉም ከፍ ያለ እና ጥልቅ የሕይወት መሥዋዕትነት ዋጋ የተከፈለበት ነው።
በነገው ዕለት በብሔራዊ ደረጃ የሚከበረው 19ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ኢትዮጵያውያን የነፃነታቸውን እና የክብራቸውን ማኅተም እያሰቡ ለአንድነታቸው እና ለሀገራዊ ሕዳሴያቸው የገቡትን ቃል የሚያድሱበት ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 መሠረት በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰኞ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን፣ ዘንድሮ “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
"የተፈጥሮ ፀጋ የጀግና ሕዝብ እናት፤ እንጠብቅሻለን አለብን አደራ፣ ኢትዮጵያችን ኑሪ እኛም ባንቺ እንኩራ!" የሚለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ማጠቃለያ ስንኝ፣ የኢትዮጵያውያንን የትናንት፣ የዛሬና የነገ የቃል ኪዳን ገመድ በሰንደቅ ዓላማቸው ሥር የሚያስተሳስር ሀገራዊ ጥሪ ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለነፃነቷ እና ለሰንደቅ ዓላማዋ ክብር ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ አያሌ የጀግኖች አባቶች እና እናቶች ሀገር በመሆኗ ይህ አደራ የትውልድ ቅብብሎሽ ሆኖ ይቀጥላል።
ከጥንታዊ አባት ዐርበኞች እስከ አሁኑ ዘመናዊና ጽኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ድረስ ያለው ታሪካዊ የጀግንነት ቅብብሎሽ የመነጨው ከዚሁ የሰንደቅ ዓላማ አደራ ነው።
የሀገራችን የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና የፀሐይ መውጫና መግቢያ ድንበሮቻችንን የሚያስጠብቁ ጀግኖች ይህችን ሰንደቅ ዓላማ በከፍታ ላይ በማውለብለብ በየግንባሩ መስዋዕትነት የሚከፍሉት ለሀገር ክብር ሲሉ ነው።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመካከል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ ብሔራዊ ዓርማ አለው።
አረንጓዴው ቀለም ልምላሜን፣ የተፈጥሮ ሀብትን እና የልማት ተስፋን ሲያበስር፤ ቢጫው እምነትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን ያንጸባርቃል።
ቀዩ ቀለም ደግሞ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝቦች ነፃነት ሲባል በጀግኖች የተከፈለውን የደም መስዋዕትነትና ጽናት የሚያሳይ ነው።
በመካከሉ ያለው ሰማያዊ መደብ እና ብሩህ ኮከብ የሕዝቦችን እኩልነት፣ አንድነትና ብሩህ የወደፊት ተስፋ የሚያመለክት የሕዝቦች ብሔራዊ መግባባት ማኅተም ነው።
በነገው ዕለት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከበረው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በይፋዊ ንግግር በዓሉን የሚያስጀምሩ ሲሆን፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መሪነትም በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎች በሰንደቅ ዓላማው ፊት የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ይፈጽማሉ።
በይፋዊው የሰንቅ ዓላማ ማውለብለብ ሥነ ሥርዓት ላይም የመከላከያ ሠራዊት ማርሽ ባንድ እና ክብር ዘብ፣ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዐርበኞች ማኅበር እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ።
በመሆኑም ይህ ዕለት በቃላት ከሚገለጽ በዓል በላይ የወደፊት ብልጽግናችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለመትከል፣ ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከርና የጋራ ሀገራችንን በሰላም እና በልማት ከፍ ለማድረግ የምንገባው አዲስ ቃል ኪዳን ነው።
ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነታችን ምስክር፣ የሕዳሴያችን መሪ እና የነገዋ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ማዕዘን ሆኖ ለዘላለም በከፍታ ላይ ይውለበለባል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: