ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳመለከቱት ተቋሙ የተሟላ የአየር ትንበያ አገልግሎት በመስጠት ለሀገራችን ልማት እና አቅም ወሳኝ ሥራዎችን የሚያከናውን የረጅም ዘመን ዕድሜ ያለው ተቋም ነው።
ጉብኝቱ እየተለዋወጠ ያለውን የአየር ፀባይ እና የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ለመረዳት እና ምላሽ ለመስጠት ያለንን አቅም ለማጠናከር ሚቲዎሮሎጂያዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የሳይንሳዊ ምርምር እና የቴክኖሎጂ ዕድገት ያለውን የላቀ ጠቀሜታ ያረጋገጠ ሆኖ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማትን ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ግብርና፣ ውኃ፣ ጤና፣ አቪዬሽን እና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን ጨምሮ ቁልፍ ዘርፎች የሚደገፉባቸውን አገልግሎቶች ለማሻሻል በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና በመረጃ መሠረተ-ልማት ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም አደጋዎችን አስቀድሞ በመተንበይ የትኞቹ አካባቢዎች ላይ ጣልቃ ገብነት ይበልጥ እንደሚያስፈልግ ለመወሰን፣ እንዲሁም ወቅታዊ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመንቀሳቀስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ያላቸው ጠቀሜታ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አስተማማኝ መረጃ ወደ ተግባራዊ መመሪያዎች ሲቀየር ሕይወትን እንደሚታደግ፣ ሀብትን እንደሚጠብቅ እና የተሻለ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያግዝም አክለው ገልጸዋል።
ይህ ዓይነቱ ሥራ ከሳተላይት ምልከታ ያለፈ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ሥራው መረጃዎች ተሰብስበው፣ ተቀናብረው እና ተተንትነው ወቅታዊ እርምጃ ለመውሰድ እንዲያግዙ በመላ ኢትዮጵያ ባሉ ጠንካራ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እና የመረጃ ማዕከላት መረብ ላይ ጭምር የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: