Search

የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ከአፋኙ የህወሓት አገዛዝ ነፃ በመውጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ

ማክሰኞ ጥቅምት 03, 2019 67

የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የህወሓት ቡድን ለዘመናት የትግራይን ሕዝብ ለገዛ ጥቅሙ ሲል ለአደጋ ሲዳርግ እና ወጣቱን ለጦርነት ሲማግድ መቆየቱን በመግለጽ፣ አሁን ላይ የሰላም አየር መንፈስ በመጀመሩ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገለጹ። 

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ቡድኑ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመጥቀም ሳይሆን ከባዕዳን ኃይሎች ጋር በጥቅም መተሳሰር መለያው እንደሆነ እና ወጣቱን እየማገደ ሥልጣኑን ለማራዘም ሲሰራ ቆይቷል።

በተለይም ከፌደራል መንግሥት ካፈነገጠ በኋላ የወጣቱን ዕድሜ እና ከዓለም ጋር እኩል የመራመድ ተስፋውን ሲነጥቅ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በግዳጅ ወደ ጦር ሜዳ ከተወሰዱት ወጣቶች እና ሕፃናት መካከል የተመለሰ እንደሌለ እና ነባር አባላቱ ብቻ መመለሳቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ሕዝቡ ለዓመታት በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖር መደረጉን አመልክተዋል።

ቡድኑ አሁናዊውን የጂኦፖለቲካ ሁኔታ ባለመረዳት ኢትዮጵያን እና የትግራይን ሕዝብ በውክልና ጦርነት ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ ታሪካዊ ጠላትነቱን ማረጋገጡንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሥልጣን በነበረበት ዘመንም ቢሆን ከአመራሮቹ እና ከዘመዶቻቸው በስተቀር ለትግራይ ሕዝብ አንዳች ጠብ ያለ ልማት አላመጣም፡፡ ወጣቱን የሥልጣን ማስጠበቂያ በማድረግ እናቶች የወላድ መካን እንዲሆኑ እንዲሁም ሕዝቡ አርሶ እና ነግዶ መኖር እንዳይችል አድርጓል ብለዋል።

አሁን ላይ በመላው ትግራይ የሰላም አየር እየነፈሰ መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ ለረጅም ጊዜ በውስጣቸው ታፍኖ የቆየው ኢትዮጵያዊነት ገንፍሎ በመውጣቱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በከተሞች ላይ ማውለብለባቸውን እና ለፌደራል መንግሥት ያላቸውን ድጋፍ ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት፣ ነዋሪው ሰላም አግኝቶ በሰላም ወደ ቤቱ የሚገባ ከሆነ ከዚህ የሚበልጥ ደስታ እንደሌለ ገልጸው፣ ከጨቋኝ ስርዓት በመውጣታቸው እና ሰላም በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ቡድኑ ከሕዝቡ ጋር አንድ እንደሆነ ለማሳመን ቢጥርም የአድጉዶም ነዋሪዎች በአደባባይ ወጥተው በተቃራኒው መቆማቸውን አስመስክረዋል።

ነዋሪዎቹ የኤርትራ መንግሥት ጣልቃ ገብነትንም ሆነ የህወሓትን አፋኝ አገዛዝ አንፈልግም በማለት እውነተኛ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በጋራ በመደመር የልማት ፀጋዎችን የመቋደስ፣ ወጣቶች በነጻነት እየተንቀሳቀሱ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ እና ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ የሚሆኑበት አዲስ የልማት ምዕራፍ መጀመሩንም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: