Search

"የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለቀጣይ ትውልዶች የሚተላለፍ ሳይሆን፣ አሁን ባለው ትውልድ እውን ሊሆን የሚገባው የህልውና ጉዳይ ነው" - የማኅበረሰብ አንቂ ዛሒድ ዘይዳን

ማክሰኞ ጥቅምት 03, 2019 73

ኢትዮጵያ ለባሕር በር ጥያቄዋ ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በዓለም አቀፍ መድረኮች ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች።

በዚህ የዲፕሎማሲ እና የሉዓላዊነት ተጋድሎ ውስጥ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ባለሙያዎች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

የማኅበረሰብ አንቂው ዛሒድ ዘይዳን ባለፉት 15 ዓመታት በዐረብኛ ቋንቋ የኢትዮጵያን እውነተኛ አቋም እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በጽናት ሲሟገቱ ከቆዩ ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው።

የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ እና የወደፊት አቅጣጫ ለዐረቡ ዓለም ሕዝቦች የማድረስ አስፈላጊነትን በመረዳት በዓረብኛ ቋንቋ በሚደረግ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ላይ አተኩረው እየሠሩ ይገኛሉ።

የሀገር ፍቅር እና የዲፕሎማሲ ግንዛቤ ገና ከመዋለ ሕፃናት ጀምሮ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ መካተት እንዳለበት የሚያስረዱት አንቂው፣ የኢትዮጵያን አንድነት እና ታሪካዊ ተምሳሌትነት በዐረብኛ ቋንቋ ጭምር ማሳወቅ ወሳኝ እንደሆነ ያመላክታሉ።

ትምህርት ቤቶችን የማኅበረሰብ ማዕከል በማድረግ ዜጎች የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲያዳብሩ ማድረግ ለሀገራዊ ዲፕሎማሲ ግንባታ ትልቅ መሠረት እንደሆነ ይገልጻሉ።

እንደ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ጠቃሜታ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለቀጣዩ ትውልድ ማስረፅ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ቀጠሮ ሳይሆን፣ አሁን ባለው ትውልድ እውን ሊሆን የሚገባው የህልውና ጉዳይ በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ለዚህ ስኬት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ።

በዓባይ ወንዝ ላይ ፍጹም የብቸኝነት መብት ለማረጋገጥ የምትሠራው ግብፅ ኢትዮጵያን ከልማት ለማስተጓጎል የተለያዩ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ሴራዎችን ስትጎነጉን ኖራለች።

ዓባይን የፖለቲካ መሣሪያ በማድረግ በዐረብ ሊግም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን የማዳከም ጥረቷን አሁንም ቀጥላለች።

ሆኖም ግብፅ የምትጠቅሳቸው የ1929 እና የ1959 የቅኝ ግዛት ውሎች የላይኛውን ተፋሰስ ሀገር ኢትዮጵያን የማይመለከቱ እና ሕጋዊ አስገዳጅነት የሌላቸው መሆናቸው የአደባባይ ምስጥር ነው።

ኢትዮጵያ ስለሕዳሴ ግድብ እስከ አሁን ድረስ ግልጽነት በተሞላበት መንገድ መረጃዎችን ስታጋራ የቆየች ሲሆን፣ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የተፈጥሮ ሀብታቸውን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላቸው በሕዳሴ ግድቧ ግንባታ አረጋግጣለች።

የግድቡ ግንባታ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስም በተግባር ተረጋግጧል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምሰሶ ሀገር እንደ መሆኗ መጠን ቀጣናዊ ትስስርን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጉዞ በየትኛውም ውጫዊ ጫና ወይም የዲፕሎማሲ ሴራ ሊቆም አይችልም።

በአሁኑ ወቅት ለጅቡቲ ወደብ የሚከፈለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታሳቢ ሲደረግ፣ የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የህልውና ያህል ወሳኝ ነው።

የቀጥታ የባሕር በር ማግኘት ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ደጋፊ በመሆኑ ለወደብ ክራይ የሚወጣውን ወጪ በሀገር ውስጥ ልማት ላይ በማዋል የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል ያስችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የባሕር በር የማግኘት መብቷን በዚህ ትውልድ እንደምታረጋግጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የሰጥቶ መቀበል መርሕን መሠረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን የምታካፍል እና በጋራ ለማደግ የምትፈልግ መሆኗን ስታስመሰክር፣ በምላሹ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ በሰላማዊ እና ፍትሐዊ መንገድ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተውበታል።

እንደ ማኅበረሰብ አንቂው ዛሒድ ዘይዳን ያሉ የማኅበረሰብ ዲፕሎማሲ ተሟጋቾች ጥረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጽኑ አቋም ጋር ተቀናጅቶ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አስከብራ በዓለም አቀፍ እና በቀጣናዊ መድረኮች ያላት ተሰሚነት ከፍ ማለቱ የማይቀር ነው።

#የመደመርመንግሥት #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በላሉ ኢታላ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: