Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት፡- ከሀገራዊ ልማት እስከ ቀጣናዊ የጋራ ብልጽግና እና ሰላም

ረቡዕ ጥቅምት 04, 2019 67

የአፍሪካ ቀንድ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የጂኦ-ፖለቲካ እና የጂኦ-ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ማዕከል እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ስትራቴጂያዊ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጎልቶ እየወጣ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላትና በአፍሪካ ፈጣን ከሚባሉት ኢኮኖሚዎች አንዷ ብትሆንም፣ ቀጥተኛ የባሕር በር የሌላት በዓለም ላይ ትልቋ ሀገር ናት።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የራሷን የገቢና ወጪ ንግድ የማስፋፋት እና የሎጂስቲክስ ወጪን የመቀነስ ፍላጎት ብቻ ያካተተ አይደለም፤ ይልቁንም የአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባሕር ቀጣናን ዘላቂ ሰላም፣ የኢኮኖሚ ትስስር፣ የጋራ ደኅንነት እና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ትልቅ ስትራቴጂያዊ ዕድል ነው።

የኢትዮጵያ ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የኢኮኖሚ መስፋፋት ቀጥተኛና አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት የሕልውና ያህል ወሳኝ ያደርገዋል። ከ130 ሚሊዮን በላይ የሚሆን አምራችና ተጠቃሚ ሕዝብ ያላት ሀገር፣ ምርቷን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብና ለኢንዱስትሪዎቿ የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባት ሰፊና አስተማማኝ የባሕር በር አማራጮች ያስፈልጓታል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለወጪ ንግዷ አብዛኛውን ወጪ የምታደርገው ለወደብ አገልግሎት ክፍያ ሲሆን፣ ይህ ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪ በሀገራችን የንግድ ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ ለቀጣናው ኢኮኖሚም የሀብት ፍሰት መደናቀፍን ይፈጥራል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ማዕከላዊ ስፍራ ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት የጂኦግራፊያዊ ትስስር ለቀጣናዊ የንግድና የትራንስፖርት ማዕከልነት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ለዓለም አቀፍ ንግድ፣ ለኢነርጂ አቅርቦት እና ለባሕር ላይ ደኅንነት እጅግ ወሳኝ የሆኑ የመርከብ መስመሮች ናቸው።

በዚሁ አካባቢ የሚታዩ የባሕር ላይ ወንብድናዎች፣ ሕገ-ወጥ ዝውውሮችና የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረቶች የዓለም አቀፍ ንግድ ስጋት በመሆናቸው፣ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ የጸጥታና የደኅንነት አቅም ያላት ኢትዮጵያ በባሕር በር ባለቤትነት በቀጣናው ሰላም ላይ ቀጥተኛ ድርሻ ማድረጓ የባሕር መስመሮቹን ደኅንነት ለማስጠበቅ ትልቅ አቅም ይሆናል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ ታዳሽ የኃይል አቅርቦት ለጎረቤት ሀገራት በማቅረብ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ የባሕር በር ማግኘትና የወደብ መሠረተ ልማት ትስስር መፍጠር ይህንን የኢነርጂና የሸቀጦች አቅርቦት ዋስትና የበለጠ በማጠናከር ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ያፋጥነዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ከግጭትና ከውድድር ይልቅ በጋራ ጥቅም፣ በዲፕሎማሲ እና በሰላማዊ ውይይት ላይ የተመሠረተ እና የቀጣናውን የጋራ ዕድገትና ሰላም የሚያፋጥን ስትራቴጂያዊ መሳርያ ነው። የኢትዮጵያን ሀገራዊ ጥቅም ከቀጣናዊ የጋራ ብልጽግና ጋር በማጣጣም የባሕር በር ጥያቄን መመለስ፣ ለአፍሪካ ቀንድ አዲስ የሰላም፣ የትብብር እና የዘላቂ ልማት ምዕራፍ የሚከፍት ወሳኝ ዕድል ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: