ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በዲፕሎማሲ እና በሕዝብ ብዛት በአፍሪካ ቀንድ ያላት ቁልፍ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የባሕር በር ባለቤት መሆን አለመቻሏ ለኢኮኖሚና ለሕልውናዋ ከፍተኛ ፈተና ሆኖባት ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከወጪ ንግዷ እስከ 95 በመቶ የሚሆነውን በጅቡቲ ወደብ ብቻ የምታስተናግድ በመሆኑ የሎጂስቲክስ እና የደኅንነት ተጋላጭነቷ ከፍተኛ ነው።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ሰለሞን አሊ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋትና እያደገ ካለው የኢኮኖሚ ፍላጎት አንጻር እንደ ምጽዋ፣ ፖርት ሱዳን፣ ላሙ እና በርበራ ያሉ በርካታ ወደቦችን በአማራጭነት መጠቀም እስከ 2050 ላለው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ወሳኝ ነው።
ወደብ አልባ መሆን በአንድ ኮንቴነር ትራንስፖርት ላይ ብቻ እጅግ ከፍተኛ ወጪ እንዲወጣ በማድረግ በዜጎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያስከተለ ይገኛል ብለዋል።
የውሃ ሃብት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ምህረት ደናንቶም በበኩላቸው፣ የባሕር በር ማጣት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በነፍስ ወከፍ በዓመት እስከ 35 ሺህ ብር ተጨማሪ ወጪ እንዲከፍል እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በሕግና በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ጥያቄዋን ማንሳቷ የቀጣናውን ሰላምና ትብብር የሚያረጋግጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ የቀጣናው ሀገራት ሀብታቸውን በጋራ በመጠቀም ዕድገታቸው ለማረጋገጥ ወሳኝና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ምሁራን አስገንዝበዋል።
#የመደመርመንግሥት #ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: