የጥፋት ኃይሎችን የሴራ መዋቅር በማፍረስ ወደ ታላቋ ኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ባለቤትነት የተሸጋገረበት ታሪካዊ የእፎይታ ምዕራፍ ጀምሯል።
በትግራይ ክልል ለረጅም ዓመታት ሰፍኖ የነበረው አምባገነናዊ ጭቆናና የፖለቲካ ጽልመት በማኅበረሰቡ ቁርጠኝነትና ሕዝባዊ እምቢተኝነት በተገኘ ታሪካዊ ውጤት አዲስ የሰላም ብርሃን ፈንጥቆበታል።
የትግራይ ሕዝብና ወጣቶች ያካሄዱት ያልተቋረጠ የመብትና የነፃነት ትግል በሕዝብ ስቃይ ሲነግድ የቆየውን የሕወኃት ስብስብ ወሰን ለሌለው የፖለቲካና የሞራል ክስረት ዳርጎታል።
ሕገ-ወጡ ቡድን በሕዝባዊ እምቢተኝነት ማዕበል ተሸንፎና ተዋርዶ ከመድረኩ ሲወገድ በትግራይ ከተሞችና አደባባዮች የታየው አጠቃላይ የደስታና የእፎይታ ማዕበል ቀላል ታሪካዊ ክስተት አይደለም።
ይህ ታላቅ ሕዝብ ለረጅም አሥርታት ያህል የጽንፈኛ የፖለቲካ ቁማርተኞች መሸጫ ሸቀጥ የጦርነት ማገዶ እና የመደራደሪያ ታጋች ሆኖ ከመቆየት መላቀቁን በተግባር ያወጀበት ታሪካዊ መታጠፊያ ነው።
ይህ ታሪካዊ ሽግግር የትግራይ ሕዝብ የሰላም፣ የልማትና የታላቋ ኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ባለቤትና ግንባር ቀደም አምድ መሆኑን ዳግም ያስመሰከረ አዲስ ምዕራፍ ሆኗል።
ይህን አገራዊና ቀጠናዊ የፖሊሲ ሂደት በወሳኝ የጂኦፖለቲካ መነጽር ስንመረምረው በትግራይ ወጣቶች ዘንድ የተፈጠረው ሥነ-ልቦናዊ ንቃት የህገ ወጡ ሕወኃትን የሐሰት ትርክት ከሥረ-መሠረቱ የደረመሰ መዋቅራዊ ኃይል ሆኖ እናገኘዋለን።
ወጣቱ “ከእንግዲህ ለፖለቲከኞች የሆድ ፍላጎት መጠቀሚያና ለጥፋት አጀንዳቸው ማገዶ አንሆንም” በሚል ጽኑ አቋም በመቆም ከጦርነት ወደ ትምህርት ገበታ፣ ወደ ሥራና የልማት ማዕድ የመመለስ ውሳኔውን አረጋግጧል።
በተቃራኒው የከሰረው የህገወጡ ሕወኃት ስብስብ ርዝራዦች የፈጸሙት ታሪካዊ ክህደት የቡድኑን እውነተኛ እርቃን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ አድርጓል።
ትላንት የትግራይን ወጣት በግፍ ሲያስጨፈጭፍበት የነበረውንና “ታሪካዊ ጠላቴ” ሲል የፈረጀውን የሻዕቢያ ስብስብ ሥር በመደፋት የገዛ ወገኑን ወግቶ ኤርትራን እንደ አዳኝ አድርጎ ተቀብሏል።
ከዚህም በላይ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ለማጨናገፍ እና በሁለቱ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን በአባይ እና በቀይ ባሕር ላይ የተቃጣውን አገራዊ ሕልውናን የማተራመስ የግብፅና የታሪካዊ ጠላቶች የጥፋት ተልዕኮ ተራ ጉዳይ ፈጻሚ እና ተቀጣሪ ሆኖ መቆየቱ የቡድኑን የውጭ ተላላኪነት በግልጽ አሳይቷል።
ነገር ግን የትግራይ ሕዝብ ከዚህ የጥፋት ቡድን አዛዥነት ሲላቀቅ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር አብሮ የመልማት፣ የማደግና የሀገር ባለቤት የመሆን ጽኑ ፍላጎቱን አረጋግጧል።
የባሕር በር አጀንዳን ጨምሮ በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው አቋም የትግራይ ሕዝብ ታሪክን ያጸና፣ ለሀገር ሕልውና ውድ ዋጋ የከፈለና አሁንም የኢትዮጵያዊነት የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ያረጋገጠበት ነው።
የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልል ልክ እንደ ሌሎች የሀገራችን ክፍሎች የሰላም፣ የልማትና የሕዳሴ ማዕከል እንዲሆን የወሰዳቸው እርምጃዎች በባዶ ቃላት ሳይሆን በፖሊሲ የተደገፉ በተጨባጭ ተግባራት የታጀቡ ናቸው።
መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ በተግባር በመተርጎም የቀደሙ ታጣቂዎችን ከጦርነት መስክ አውጥቶ ወደ ሰላማዊና ምርታማ የማኅበረሰብ ሕይወት የመመለስ መዋቅራዊ እርምጃ በመውሰድ በትግራይ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የተሃድሶ ቅበላ ማዕከላትን አደራጅቷል፤ ይህም የተራዘመውን የግጭት አዙሪት የመስበር ሚና ይጫወታል።
በተመሳሳይ መልኩ በአላማጣ ከተማ በችግር ውስጥ ለወደቁ ዜጎች በፍጥነት አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ የዜግነት አለኝታነትንና የሰብዓዊ ኃላፊነትን በተግባር ያረጋገጠ ሲሆን፣ ከዚህም ጎን ለጎን የአዲስ አበባ መቐለ የአየር በረራ ዳግም መጀመሩ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለማነቃቃት፣ የማኅበረሰብ ትስስርን መልሶ ለመገንባትና አገልግሎቶችን ለማፋጠን ታላቅ ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አበርክቷል።
በመቐለና በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የተሃድሶ ማዕከላት መከፈት፣ ለተጎጂዎች በቀጥታ የሰብዓዊ ድጋፍ መድረስ እና የአየር ትራንስፖርት ትስስር ዳግም መጀመር የሚያረጋግጡት ትልቁ እውነት ሰላም በፖለቲካ መግለጫ ሳይሆን በተግባራዊ የልማት ሥራዎች የሚገነባ መሆኑን ነው።
የትግራይ ሕዝብ ከህገ ወጡ ሕወኃት የዘመናት የስቃይ ቀንበርና የፖለቲካ መጫወቻነት በመላቀቅ ያሳየው እፎይታና አገራዊ ወገንተኝነት፣ የጥፋት ኃይሎችን የሴራ መዋቅር ያፈረሰ ትልቅ ውሳኔ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ ሀገር የማጸናትና የማቆም ሚናውን በማደስ፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቹ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ወደ ልማትና ወደ ላቀ ብልፅግና መሸጋገሩ፣ የዜጎችን ሕይወት ከመታደግ ባለፈ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ሕልውና፣ ሉዓላዊነትና የጋራ የወደፊት ተስፋ ለማጠናከር ወሳኝ እና አማራጭ የሌለው አገራዊ ጎዳና ሆኖ ይቀጥላል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: