Search

ዓለም አቀፉ የሴት አርሶና አርብቶ አደሮች ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ ነው

ሓሙስ ጥቅምት 05, 2019 48

ዓለም አቀፉ የሴት አርሶ እና አርብቶ አደሮች ቀን በየዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን እንዲከበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) የወሰነው እ.አ.አ በ2007 ነው፡፡

የዕለቱ ዋና ዓላማ በገጠር የሚኖሩ ሴቶች ለምግብ ዋስትና፣ ለግብርና እድገት እና ለድህነት ቅነሳ የሚያበረክቱትን የማይተካ አስተዋጽኦ እውቅና መስጠትና ማክበር ነው፡፡

በዚህም መሠረት ቀኑ በኢትዮጵያ “ሴት አርሶ እና አርብቶ አደሮችን እናብቃ፤ የምግብ ዋስትናን እናረጋግጥ፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአነስተኛ ይዞታ እስከ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ድረስ በመሰማራት ውጤት ያስመዘገቡ ሴት አርሶ እና አርብቶ አደሮች መኖራቸውን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ሴቶች ከዚህ የበለጠ ጠንካራ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያጋጥሟቸውን የባንክ ብድር ውስንነት፣ የመሬት ባለቤትነት እና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ችግሮች ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሴት አርሶ እና አርብቶ አደሮችን መደገፍና ማበረታታት የሴቶችን የሀብት ባለቤትነት እና የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ፣ አምራችነትን የሚያሳድግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚረዳ እንዲሁም የገጠር የኢኮኖሚ ሽግግርን የሚያፋጥን ነው፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ ባለው በዚህ ዕለት በመሬት አጠቃቀም፣ ይዞታ እና ተያያዥ የሕግ ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የተካሄደ ሲሆን፣ በግብርና መካናይዜሽን ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች የሚሆኑ የግብርና መሣሪያዎች ስጦታ ተበርክቷል፡፡

#የመደመርመንግሥት #ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ

በሰናይት ብርሃኔ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: