የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው 3ኛ መደበኛ ጉባኤው የምክር ቤቱን ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ሰይሟል።
አፈ ጉባኤ አቶ አሕመድ ሽዴ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ተከትሎ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ምክር ቤቱ በይፋ መከፈቱን አስታውሰዋል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55/19 መሠረትም ለምክር ቤቱ የሚያስፈልጉ ቋሚ እና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን ማዋቀር እንደሚገባ በሕግ መደነገጉን ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 152 መሠረት ምክር ቤቱ ሲመሠረት ከሚቋቋሙት ኮሚቴዎች መካከል የምክር ቤቱን አጀንዳ የሚያዘጋጅ፣ ዓመታዊ በጀት የሚያቀርብ፣ የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ እና የንብረት አስተዳደርን የሚከታተል እና የሚቆጣጠር እንዲሁም የምክር ቤቱን ደንብ የሚተረጉም እና አፈጻጸሙን የሚያግዙ መመሪያዎችን የሚያወጣ አማካሪ ኮሚቴ ይገኝበታል።
ኮሚቴው በዚሁ ደንብ አንቀጽ 152/1 መሠረት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ እና የፓርቲ ተጠሪዎችን ጨምሮ የፓርላማ ቡድኖች ባላቸው የመቀመጫ መጠን የሚወከሉበት እና በአፈ ጉባኤው የሚመራ መሆኑ ይታወቃል።
አፈ ጉባኤ አቶ አህመድ ሽዴ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ፣ በእጩዎች አመራረጥ ወቅት ከመንግሥት ተጠሪ እና ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
አሠራሩም ብዝኃነትን፣ ብቃትን፣ የሥራ ልምድን፣ በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸውን የተፎካካሪ ፓርቲዎች ውክልና፣ እንዲሁም የአዳዲስ እና የነባር አባላትን ጥምረት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት የኮሚቴው አባላት፡-
1. የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ
2. የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ
3. በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ
4. በምክር ቤቱ ሁለት ረዳት የመንግሥት ተጠሪዎች
5. ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ
6. አቶ አብዱ ሐሰን
7. ዶክተር ጥላሁን አርዱኖ
8. ዶክተር ካሳሁን ደለነ
9. አቶ የሱፍ ኢብራሂም
10. አቶ ዝኑር አብዱልዋሂብ
11. ወ/ሮ ፈተና ባዩ
12. አቶ ለገሰ ላንቃሞ
ሆነው ተሰይመዋል፡፡
ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55/19 እና በደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 152 መሠረት የቀረበውን የምክር ቤቱ ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ አባላት የመሰየም ውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 2/2019 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል፡፡
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: