Search

ተቋማትን በማውደም የሕዝብ ጠላት መሆኑን ዳግም ያረጋገጠው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን

ሓሙስ ጥቅምት 05, 2019 53

ከሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ነፃ የወጣችው የመቐለ ከተማ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች ትገኛለች።

ቡድኑ ከከተማዋ በሚወጣበት ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች እና በመንግሥት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት እና ዝርፊያ ፈጽሞ መሸሹ ተመላክቷል።

በተለይም በትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ግቢ እና ሕንፃ ውስጥ በቡድኑ እና በጀሌዎቹ ከፍተኛ ውድመት እና ዝርፊያ መፈጸሙን ኢቢሲ በስፍራው ተገኝቶ አረጋግጧል።

በጽሕፈት ቤቱ ግቢ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የመንግሥት እና የሕዝብ ንብረቶች ተዘበራርቀው እንዲሁም የተሽከርካሪዎች ጎማዎች ተሰርቀው እና ተሰባብረው ይታያሉ። በሕንፃው የውስጥ ክፍሎች ላይ የደረሰው ውድመትም የከፋ ነው።

በጽሕፈት ቤቱ ውስጥ በሁለተኛ፣ በሦስተኛ እና በአራተኛ ወለሎች ላይ በሚገኙ ቢሮዎች፦

• በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያወጡ ኮምፒውተሮች፣ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች እና ሌሎች ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ንብረቶች በየሜዳው እና በኮሪደሮች ላይ ተሰባብረው ይገኛሉ።

• በርካታ የፋይናንስ ሰነዶች፣ ካዝናዎች እና የኢትዮጵያ የገንዘብ ኖት ለውድመት እና ለዝርፊያ ተዳርገዋል።

• ለሕዝብ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የሰርቨር መሣሪያዎች ተነቃቅለው የተወሰዱ ሲሆን፣ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዳይሰጥ ተደርጓል። ይህ ሁሉ እኩይ ድርጊት የቡድኑን ጸረ ሕዝብነት የሚያሳይ ነው።

በሕንፃው አራተኛ ወለል ላይ የሚገኘው የርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ ከፍተኛ ውድመት ካስተናገዱ ክፍሎች አንዱ ነው። በርካታ ታሪካዊ እና ወሳኝ የሆኑ የመንግሥት ሰነዶች የሚገኙበት ይህ ቢሮ፣ በቡድኑ አማካይነት መረጃዎችን ለማጥፋት እና ንብረት ለመዝረፍ ታስቦ ከፍተኛ ጥቃት እንደተፈጸመበት ታይቷል።

ታዛቢዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ሕገ ወጡ ቡድን ላለፉት አምስት ዐሥርተ ዓመታት የትግራይን፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር ሲዳርግ የቆየ ሲሆን፣ አሁን የሕዝብ መገልገያ የሆኑ ተቋማትን እና ሀብቶችን ማውደሙ እና መዝረፉ ቡድኑ የሕዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር ያረጋገጠበት ክስተት ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የመደበኛ አገልግሎቶች አሰጣጥን ወደ ነበረበት ለመመለስ እና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: