የትግራይ ክልል የባለአደራ አስተዳደር ሕዝባዊ አገልግሎቶችን የማነቃቃት ተግባርን በቀዳሚነት እንደሚወጣ የመቐለ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 ዓ.ም አንቀጽ 14 (2) (ለ) መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የኢፌዴሪ መንግሥት የትግራይ ክልልን የሚያጸና ውሳኔ ወስኗል።
በዚህም የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ትግራይን የሚያስተዳድር ይሆናል።
የባለአደራ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት ማድረግ ይጠበቅበታል።
በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስክሚቋቋም ድረስ የክልሉን የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች ከማቅረብና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር በዘለለ፣ ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ አንድምታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ እንደማይንቀሳቀስ ተገልጿል። ባለአደራ አስተዳደሩም ተግባሩን ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና መመሪያ መሠረት ያከናውናል።
በባለአደራ አስተዳደሩ የመቐለ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሕገ ወጡ የህወሐት ቡድን የጥፋት እና የቁማር ፖለቲካ ለመጨረሻ ጊዜ አብቅቷል።
የተቋቋመው ባለአደራ አስተዳደር ዋና እና ቀዳሚ ተግባሩ ሰላምና ማረጋጋት በማስፈን መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶችንና መሠረተ ልማቶችን ማጠናከር መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ተግባር በብቃት ለመወጣት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ቀያቸው መመለስ እና ኢኮኖሚውን ማነቃቃትም ባለአደራ አስተዳደሩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው ብለዋል።
የትግራይ ክልል ሕዝብ የዴሞክራሲ ሥርዓትን፣ እኩልነት እና ፍትሕን ለማረጋገጥ ለረጅም ጊዜ ዋጋ ከፍሏል ያሉት ዶክተር ሽሻይ፤ በቀጣይም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እና ሕዝቡ በመረጠው መንግሥት እንዲተዳደር ለማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ ሕጎች፣ አሠራሮች እና ውሳኔዎች በማውጣት ኃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ለቀጣይ ምርጫ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ትኩረት እንደሚሰጡም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ተልዕኮውን ለመፈጸም ከሕዝቡ፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከሚመለከታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ዶክተር ሽሻይ አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: