የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታና ፍትሕ አካላት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ኦፕሬሽን፣ በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀል በ658 ዜጎች ላይ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ያደረሱ 37 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው መሆኑን ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ በቡድን በመደራጀት የባንክ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኛ በመምሰል፦ "ሽልማት ደርሶዎታል"፣ "የሞባይል ባንኪንግ ሥርዓት ልናዘምንልዎት ነው"፣ "የባንክ ሒሳብዎን ከፋይዳ መታወቂያዎ ጋር ለማስተሳሰር ነው" በሚል ስልክ በመደወል የይለፍ ቃል፣ OTP፣ PIN ወይም ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን በመጠየቅ እና የተለያዩ ማጭበርበሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሲያጭበረብሩ እንደነበር ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል።
ተጠርጣሪዎቹ በቡድን ተደራጅተው መኖሪያ ቤት በመከራየት፣ በተለያዩ ሰዎች ስም የወጡ በርካታ የባንክ አካውንቶችና ሲም ካርዶችን ከግለሰቦች በመግዛት እና በመከራየት የወንጀል ተግባሩን ይፈጽሙ እንደነበር ፖሊስ በምርመራ ደርሶበታል።
ተጠርጣሪዎቹ ለወንጀል ተግባሩ ይገለገሉበት ከነበረው ዘጠኝ ተሽከርካሪዎች፣ አንድ ሞተር ሳይክል፣ 114 የሞባይል ቀፎዎች እና 478 ሲም ካርዶች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀልን ለመከላከል የጀመረውን ኦፕሬሽን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጾ፤ በአጭበርባሪዎቹ ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም ሰው፦ በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ በነፃ የስልክ መስመር (991)፣ በሰው አልባ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ (SPS) በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ በአካል በመቅረብ ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ባንኮች በግል ስልክ በመደወል ምንም ዓይነት አገልግሎት እንደማይሰጡ ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ፣ አጠራጣሪ የስልክ ጥሪዎች ሲያጋጥሙ የቀረቡለትን ጥያቄዎች አምኖና ተቀብሎ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ጉዳዩን ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይም ለባንክ ማሳወቅ እንዳለበት ፖሊስ አሳስቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: