የተለያዩ ሀገራት የወታደራዊ አታሼ አባላት በቢሾፍቱ አየር ኃይል ቤዝ በመገኘት በኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰፊ ገለጻ እና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
ከገለጻው በኋላ አታሼዎቹ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ያልተረጋገጡ እና የተሳሳቱ መረጃዎች ሲሰራጩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፉን የዲፕሎማቲክ እና የወታደራዊ አታሼ ማኅበረሰብ በመጋበዝ የሰጠው ይፋዊ እና ቀጥተኛ ገለጻ ክፍተቶችን በመድፈን ትክክለኛውን እና ወቅታዊውን መረጃ ለማግኘት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
የእንግሊዝ፣ የአውስትራሊያ፣ የባንግላዴሽ፣ የኬንያ፣ የጋቦን፣ የደቡብ ሱዳን እና የታንዛኒያ ወታደራዊ አታሼዎች በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ግዴታዋን በመወጣት የሀገሯን ሉዓላዊነት፣ የድንበር አንድነት እና የዜጎቿን ደኅንነት የማስከበር ሕጋዊ እና ተፈጥሯዊ መብት ያላት መሆኑን አረጋግጠዋል።
የባንግላዴሽ እና የታንዛኒያ ወታደራዊ አታሼዎች በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፍ የጦር ሕጎችን እና ሰብአዊ መብቶችን ጠብቆ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሠራዊቱ የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት መጠበቅ እና ሕጋዊ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አድንቀዋል።
የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን ተወካዮች በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት በቀጥታ ለጎረቤት ሀገራት እና ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጀመረው የሰላም እና የፀጥታ ማስከበር ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ መረጋጋትን እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ለምታደርገው የሰላም ጥረት ከጎኗ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የወታደራዊ አታሼ ማኅበር መሪዎች እና አባላት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክቶሬት ይህንን ግልጽ እና ወቅታዊ ማብራሪያ በማዘጋጀቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: