በትግራይ ክልል የተገኘውን ሰላም ለማጽናትና ለልማት በጋራ ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውን የውቅሮ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የከተማዋ ነዋሪዎች የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል በሕዝቡ ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጭቆናና መከራ አውግዘዋል።
በአሁኑ ወቅት ከፍርሃት ወጥተው በሰላም መንቀሳቀስ መጀመራቸውንና የሀገራዊ ልማት ተቋዳሽ ለመሆን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ባለፈው ሥርዓት ሕዝቡ በገዛ ከተማው ውስጥ እንደ እስረኛ ተገድቦ የመንቀሳቀስ፣ የመናገርና የመሥራት መብቱ ተነጥቆ በፍርሃት ውስጥ ይኖር ነበር።
ህገወጡ ህወሓት ለህዝቡ ደንታ የሌለውና ለትግራይ እናቶችና አባቶች መከራ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።
ከጦርነትና ከግጭት የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በትግራይ ክልል ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶች ሕዝቡ ሰርቶ እንዳያድግና እንዳይበለጽግ በማድረግ ከፍተኛ ማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማድረሳቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም አሁን ለትግራይ ሕዝብ የሚያስፈልገው ሰላም፣ አብሮነትና ልማት በመሆኑ፣ ያለፈው የሰቆቃ ጊዜ በቅቶን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ መሸጋገር እንፈልጋለን ብለዋል።
አሁን ያለው የፀጥታ ሁኔታ ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ መነቃቃት፣ ለልማትና ለሕዝቡ የኑሮ እንቅስቃሴ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል የልማት ኮሪደሮች መስፋፋት እንዳለባቸው ጠቅሰው ሕዝቡ የሚበጀውን አስተዳደር መርጦ ከመንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋገጠዋል።
ነዋሪዎቹ ያለችን ሀገር አንድ ኢትዮጵያ በመሆኗ፣ እያንዳንዱ ሰው ለዘላቂ ሰላም መታገልና መጠበቅ እንዳለበት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#የመደመርመንግሥት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: