Search

ብዝኃነትን በመደመር እሳቤ አስተሣሥራ ወደ ከፍታ የምትገሰግሰው ኢትዮጵያ

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 54

“ቤት በአንድ እጅ አይገነባም” የሚለው የታላቆቻችን ጥበብ የተሞላበት አባባል፣ የኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ መሠረት እና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ዋነኛ ማህተም ነው።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ባህሎች እና እምነቶች መገኛ ነች። የዚህች ታላቅ ሀገር ጥንካሬ እና ውበት የሚመነጨው ደግሞ ከተለያየ ጥበብ እና ቀለም በተሠራው የብዝኃነቷ ህብረት ነው።

ሀገር የጋራ ቤት የሚሆነው ሁሉም ሕዝቦቿ በእኩልነት፣ በመከባበር እና በጋራ ተሳትፎ ሲረባረቡ ብቻ ነው። የመደመር መንግሥት ይህንን የሀገራችንን ነባራዊ እውነት መሠረት በማድረግ ብዝኃነትን ለአንድነት እና ለጋራ ብልጽግና እንደ ትልቅ ሀብት የሚጠቀም የፖሊሲ እና የእስቤ አቅጣጫን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

የመደመር እሳቤ ዋና ማዕከል መደመር፣ መተጋገዝ እና አቅምን ማስተባበር በመሆኑ፣ የሀገራችንን የተበታተነ አቅም እና ልዩነቶች ወደ አወንታዊ የልማት ኃይል በመቀየር ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ከፍቷል። ልዩነቶችን ማጥፋት ሳይሆን የልዩነቶችን ውበት አቀናጅቶ ለሀገር ከፍታ ማዋል የመደመር መንግሥት ቁልፍ መመሪያ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገራችን እየተከናወኑ ያሉ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማቶች፣ የግብርና እና የቴክኖሎጂ አብዮቶች እንዲሁም የሀገራዊ ደኅንነት እና የሉዓላዊነት ማስከበር ሥራዎች የሁሉም ሕዝቦች የጋራ ክንድ እና የመደመር ውጤቶች ናቸው።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ እስከ አረንጓዴ ዐሻራ፣ ከሌማት ትሩፋት እስከ ዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕዮች ድረስ ያሉት ስኬቶች “ቤት በአንድ እጅ አይገነባም” የሚለውን መርሕ በመከተል በሕዝቦች የተቀናጀ አሰላለፍ እና በመደመር ዕይታ እውን የሆኑ የጋራ እውነቶች ናቸው።

ብዝኃነትን በመደመር እሳቤ ማስተሣሠር የአንዱን ስኬት የሌላው ደስታ፣ የአንዱን ፈተና ደግሞ የሁሉም የጋራ ጉዳይ አድርጎ ለመውሰድ አስችሏል።

 

የዜጎች እና የመንግሥት የማይበጠስ ኅብረት፣ የደኅንነት መዋቅሩ ሕዝባዊ መሠረት፣ እና በየአካባቢው የሚታየው ሕዝባዊ የልማት ማዕበል ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባች የፀኑ አሸናፊዎች ምድር መሆኗን በተግባር ያሳያል።

ኢትዮጵያውያን ብዝኃነታቸውን ውብ የአንድነት ዓርማ አድርገው በመያዝ፣ የመደመር መንግሥት የሚከተለውን የጋራ ብልጽግና መስመር በመከተል የታሪክ ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ በመቅረጽ ላይ ይገኛሉ።

ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር፣ ጽንፈኝነትን እና ልዩነትን የሚያሰፉ እኩይ አስተሳሰቦችን በማስወገድ፣ ሀገራችንን ወደ ላቀ የብልጽግና ማማ የማሸጋገር ጉዞ በሁሉም ልጆቿ ኅብረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: