እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የዜጎችን የጋራ ራዕይ፣ የታሪክ አረዳድ እና የወደፊት ግብ በአንድ ዐቢይ ሀገራዊ አቅጣጫ ማስተሳሰር ወሳኝ ጉዳይ ነው።
ገዥ ትርክት ሕዝብን የሚከፋፍሉ ትርክቶችን አስወግዶ፣ በሀገር ፍቅር፣ በፍትሕ እና በጋራ ዕጣ ፈንታ ላይ የተመሠረተ የጋራ ማንነት ማዕቀፍ መፍጠር ነው።
ታሪክ የትውልድ መማሪያ እንጂ የክፍፍል እና የጥርጣሬ ምንጭ መሆን የለበትም። የኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ የጋራ ድሎችን እና አብሮነትን ያጎናጸፉ ገድሎችን የያዘ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ የተከሰቱ የትርክት ቅራኔዎች ማኅበራዊ ትስስራችንን ፈትነውታል።
ዛሬ የምንፈልገው ገዥ ትርክት ያለፉትን አወዛጋቢ ታሪካዊ ክስተቶች አጣርቶና አቻችሎ፣ “በእኛ እና እነሱ” ስንጥቆች ምትክ በጋራ የሀገር ባለቤትነት ስሜት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት።
ይህ ትርክት ብዝኃነትን እንደ ሀብት በማየት የብሔር፣ የቋንቋ እና የባህል ልዩነቶች ለሀገር ውበት እና ጥንካሬ እንጂ ለመከፋፈያነት ሊውሉ እንደማይገባቸው ማመንን ይጠይቃል።
የጋራ ታሪካዊ ትሩፋቶች የሆኑ የድል ቀናትን፣ የነጻነት ዓርማዎችን እና የጋራ እሴቶችን እንደ ሀገራዊ አንድነት ማሰሪያ መጠቀም ይገባል።
የመደመር እሳቤ ልዩነቶችን አጥፍቶ አንድ ዓይነት ማድረግ ሳይሆን፣ የሁሉም ልዩነቶች ተከብረው እና እንደ ጥንካሬ ምንጭ ተቆጥረው በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ጉልበት ማደግ ነው።
መደመር ለገዥ ትርክት ግንባታ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፤ ምክንያቱም ያለፉትን መልካም እሴቶች ይዞ ወደ ፊት መራመድን ይሰብካል።
እንዲሁም በፉክክር እና በግጭት ምትክ የትብብርን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን እና የጋራ ስኬትን ባህል ይገነባል።
የትርክት ኃይል ከቃላት ባለፈ በተግባራዊ የሰው ልጆች ክብር እና ሀገር በምታስመዘግበው ኢኮኖሚያዊ ነጻነት የሚረጋገጥ ነው።
በልማት እና በፈጠራ የሰውን ሕይወት የሚቀይሩ ተጨባጭ ውጤቶች ሲመጡ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የምርታማነት ዕድገት ሲረጋገጡ፣ የዜጎች በራሳቸው እና በሀገራቸው ላይ ያላቸው እምነት ይጠነክራል።
ሕግን የሚያከብሩ፣ ፍትሕን የሚያሰፍኑ እና ለዜጎች ግልጽ አገልግሎት የሚሰጡ ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡ የሀገር ፍቅር በባዶ ቃል ሳይሆን በተግባር ይረጋገጣል።
ሰላም የልማት ሁሉ ዐቢይ መሠረት ነው። ሰላም ሲኖር ትውልዱ ጉልበቱን፣ ዕውቀቱንና ሀብቱን ወደ ፈጠራና ምርታማነት ይመራል።
በመሆኑም ግጭትን በንግግር እና በሕጋዊ መንገድ የመፍታት ልምድን ማዳበር፣ የዕድገት እና የብልጽግና ራዕይን ለአዲሱ ትውልድ በኃላፊነት ስሜት ማስተላለፍ እንዲሁም ታሪክን ባለቤትነት ባለው መንፈስ እንዲረዱ ማድረግ ገዥ ትርክትን ለመገንባት ትልቅ ሚና ይጫወታል።
የጋራ ትርክትን ማጠናከር ማለት የተለያዩ ማንነቶችን ሳያጠፋ በጋራ ሀገራዊ ዓላማ ዙሪያ ማስተሳሰር ነው።
ትርክት በፍትሕ፣ በተጠያቂነት፣ በሐቀኛ የዜጎች ተሳትፎ እና በተጨባጭ ልማታዊ ውጤቶች የሚገነባ ነው።
የዛሬን ስኬቶች ከነገው ትልቅ ራዕይ ጋር በማያያዝ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የሁላችንም የማይተካ የጋራ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: