Search

የሕዝቡን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት እንሠራለን - ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 39

በተደመረ አቅም የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት እንሠራለን ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ተናገሩ።

"በመደመር መንግሥት፤ የሕዝብ ድምፅ፣ የጋራ ተሳትፎ፣ የጋራ ልማት" በሚል መሪ ሐሳብ የሕዝብ ውይይት መድረክ ከቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተካሄደ ይገኛል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ የመደመር መንግሥት የገባውን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩ ነው።

የሕዝቡን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በጊዜ የለኝም መንፈስ በትጋት እና በቅንነት እንሠራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጥራት እና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆኑ የመንግሥት እና የሕዝብ አቅም ተሳትፎ በማጎልበት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የክልሉን ሕዝብ አብሮነት በማጠናከር ልማትን የማፋጠን ሥራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ተግባር መሆኑን ያነሡት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የቀቤና ሕዝብ ሰላም እና አንድነትን የሚያጸናበት፣ በጋራ ለመለወጥ የሚያስችል እና ዘመናትን የዘለቀ ዕሴት ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ አሚን በደዊ እንዳሉት፣ በልዩ ወረዳው ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ፣ ልምድ እና የሕዝብን የጋራ ዕሴቶች በማቀናጀት በተደመረ አቅም የመጣው ተጨባጭ ለውጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የሕዝቡን የዘመናት ጥያቄ የመደመር መንግሥት በመመለሱ ሕዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲመልስ ማድረጉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም ኅብረተሰቡ በራሱ ተነሣሽነት 657 ሚሊዮን ብር በማውጣት ሆስፒታል እየተገነባ መሆኑን ገልጸው፤ በተቀናጀ የልማት አቅም የሚተገበሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

በውይይት መርሐ ግብሩ ላይ የክልል እና የልዩ ወረዳው አስተዳደር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: