Search

"ሕገ-ወጡ ህወሓት ህልውናውን ለማስጠበቅ ሲል ህዝብን ለጦርነት እና ለችግር ሲዳርግ ቆይቷል"፡- ምሁራን

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 60

ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የራሱን እና የፓርቲውን ህልውና ለማስጠበቅ ሲል የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ መከራ፣ እንግልት እና ጦርነት ሲዳርግ መቆየቱን የሕግ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ቡድኑ በምስኪኑ ህዝብ ስም ሕገ-ወጥ የሀብት ማከማቸት እና ዝርፊያ ሲያካሂድ ቆይቷል።

በዚህም የተወሰኑ የቡድኑ አመራሮች እና ግለሰቦች ኪሳቸውን ሲያደልቡ፣ ንብረት ሲያከማቹ እና ልጆቻቸውን ውጭ ሀገር ሲያስተምሩ፣ የትግራይ ህዝብ ግን ያለ ምንም መሠረተ ልማት እና በሰላም እጦት በመከራ ውስጥ እንዲኖር ተፈርዶበታል ብለዋል።

በሌላ በኩል የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኙ አቶ ኃይለ ማርያም ይርጋ፤ ሕገ-ወጡ ህወሓት ከአመሰራረቱ ጀምሮ ከማንኛውም አጀንዳ እና የህዝብ ጥቅም በላይ ለራሱ ዓላማ እና ለፓርቲው መቀጠል ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት መርህ አልባ በሆነ መንገድ የፓርቲውን ህልውና ለማስጠበቅ ሲል ከየትኛውም የውጭ እና የውስጥ አካል ጋር ለመስራት ዝግጁ እንደነበር ጠቁመዋል።

አቶ ኃይለ ማርያም አክለውም፤ ቡድኑ ከደርግ ጋር ላደረገው የ17 ዓመት ጦርነት ከሻዕቢያ ጋር ጥምረት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ማዕከላዊ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን ከዚሁ አካል ጋር ለ7 ዓመታት ያህል በጦርነት ውስጥ ማለፉን አንስተዋል።

በተጨማሪም ህዝቡን ከዓለም እና ከዘመናዊ እድገት በመቁረጥ ኢትዮጵያ በሦስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት አልፋ ወደ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት በሚደረገው ዝግጅት ተወዳዳሪ እንዳትሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።

እንደ ግብፅ ያሉ የውጭ ኃይሎችም የኢትዮጵያን እድገት ወደ ኋላ ለመመለስ እና በወንዞቿ እንዳታደግ ለማድረግ ሕገ-ወጡን ህወሓት እንደ አጥፊ በትር ሲጠቀሙበት እንደነበር ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ አያይዘው እንዳመለከቱት፤ የትግራይ ህዝብ መንገድ፣ ኢንዱስትሪ እና ልማት ሳይገነባለት ወጣቶች ብዕር በመጨበጥ ፈንታ ቃታ እንዲስቡና ለኅዘን እንዲዳረጉ ተደርጓል።

ነገር ግን አሁን ባለው የመደመር መንግሥት ህዝብን ያስቀደመ አሰራርና ጥበብ በተሞላበት አካሄድ ህዝቡን ከቡድኑ ጭቆና የማዳንና ሀብትን ወደ ህዝብ ጥቅም የመመለስ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገልጿል።

#የመደመርመንግሥት

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: