Search

ትግራይ ከልማት የተገለለችበት ዘመን አብቅቶ ወደ አዲሱ የተስፋና የልማት ምዕራፍ ተሸጋግራለች”፦ ሞገስ ፍሥሐ (ሞጂ)

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 61

ሕገ ወጡ የሕወሓት ስብስብ የትግራይን ሕዝብ ለራሱ ሥልጣንና የግል ጥቅም ማስጠበቂያ ሲል ለዓመታት ለጦርነትና ለችግር ሲዳርገው መቆየቱን እና በአሁኑ ወቅት ግን ሕዝቡ እና ወጣቱ የቡድኑን እውነተኛ ማንነት በመረዳታቸው ከጀርባው ከመቆም መቆጠባቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪው ሞገስ ፍሥሐ (ሞጂ) ገለጸ።

ሞገስ ፍሥሐ ከኢቢሲ (EBC) ጋር በነበረው ቆይታ፣ ሕገ ወጡ ሕወሓት ከ17 ዓመታት የትግል ዘመኑ ጀምሮ የትግራይን ሕዝብ ታሪክና ምሁራን አብሮ በማጥፋት “ከእኔ ውጪ አማራጭ የለም” የሚል የተሳሳተ ትረካ ሲያሰራጭ መቆየቱን አንስቷል።

አስከፊው የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እፎይታ ካገኘ በኋላ የሕገ ወጡ ሕወሓቶች ስብስብ ሕዝቡን ወደ ሌላ ዙር እልቂት ለማስገባት የወሰዱት እርምጃ የቡድኑን የጥፋት መንገድ ግልጽ ያደረገ እንደሆነ ተናግሯል።

ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ሕዝቡ የሕገ ወጡ ሕወሓት ደጀን የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደማቅ አቀባበል እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

ሕዝቡ አሁን የመከላከያ ሠራዊቱ ዋና ደጀን በመሆን የቡድኑን እንቅስቃሴ የተደበቁ መሣሪያዎችን እና መሸሸጊያዎችን በመጠቆም ሠራዊቱ ሥራውን እንዲያከናውን ትልቅ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በተስፋና በልማት ላይ እያሉ ትግራይ ግን በሕገ ወጡ ሕወሓት እኩይ ተግባር ምክንያት ወጣት አልባ እና ከልማት የተገለለች ክልል ሆና መቆየቷን በቁጭት ያነሳው ሞገስ አሁን ባለው ሁኔታ የፌደራል መንግሥት ለክልሉ መልሶ ግንባታ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለሁለንተናዊ እድገት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ ለነበሩት አብዛኞቹ ጦርነቶችና አለመረጋጋቶች ዋና መንስኤ ሕገ ወጡ ሕወሓት እንደነበር ያነሳው ሞገስ፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ በሰላም እንድትቀጥል በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ከፌደራል መንግሥት ጎን በመቆም የጥፋትና የፀረ ሰላም ኃይሎችን ሊታገሉ እና ሊያጋልጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በትግራይ ክልል የተበሰረው የሰላም፣ የፍትሕ እና የመልሶ መገንባት አዲስ ምዕራፍ፣ ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባች #ትልቅሀገር፣ የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ አብሮነቱን ያጸና #ትልቅሕዝብ እና ለወደፊቱ የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር የሚያረጋግጥ ሲሆን ለትግራይ ሕዝብም ቀጣዩ ዘመን የነፃነት፣ የልማትና የእውነተኛ ብልጽግና የተስፋ ዘመን እንደሚሆን ያመላክታል።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: