ለትግራይ ሕዝብ ነፃነት፣ ሰላም፣ ፍትሕና ልማት እንታገላለን በሚል ተስፋ ለብዙ ዓመታት የዘለቀው የህወሓት ትርክት፣ በጊዜ ሂደት ከሰጠው ተስፋ ጋር የማይጣጣሙ ከባድ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዘዞችን አስከትሏል። በዚህ ሂደት የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ዋጋ ከፍሏል፤ በተለይም ወጣቱ ለተደጋጋሚ ግጭቶችና ለከባድ ኪሳራዎች ተዳርጓል።
የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች የተለየ የልማት፣ የሰላምና የክብር ፍላጎት የለውም። እንደማንኛውም ዜጋ በሰላም መኖር፣ ልጆቹን ማስተማር፣ በሥራው ማደግ፣ ንብረት ማፍራትና የተሻለ የወደፊት ተስፋ ማየት ይፈልጋል። ሆኖም እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለፖለቲካዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ በማዋል፣ የሕዝቡን ስሜት በማነሳሳትና ወጣቱን ወደ ግጭት በመግፋት ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻል በተግባር ታይቷል፡፡
የተደጋጋሚ ጦርነቶችና የፖለቲካ ቀውሶች ዋንኛ ገፈት ቀማሽ ሕዝብ ነው። በተለይም ወጣቱ በትምህርት፣ በሥራና በምርታማነት ሕይወቱን ከመገንባት ይልቅ ለጦርነት ሲጋለጥ፣ የሚጎዳው ግለሰቡ ብቻ ሳይሆን የአንድ ትውልድና የሀገራችን የወደፊት ተስፋም ነው። ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ የሰላም፣ የፍትሕና የልማት ፍላጎት ከማንኛውም የቡድን ጥቅምና የፖለቲካ ስሌት በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
በዚህ ረገድ የትግራይ ሕዝብ ያለፈውን ተሞክሮ በጥልቀት መመርመር፣ በፖለቲካዊ ትርክቶችና በተግባራዊ ውጤቶች መካከል ያለውን ልዩነት መለየትና የራሱን ጥቅም በራሱ የመወሰን አቅም ማጠናከር ወሳኝ ነው።
ከዚህ አንጻር ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅመው የፖለቲካ ንቃተ ሕሊና ወደ ሰላም፣ ወደ ሕዝባዊ ተሳትፎ፣ ወደ ሕግ የበላይነትና ወደ ልማት መቀየር አለበት። የሕዝቡ ድምፅ በፍርሃትና በግፊት ሳይሆን በነፃነት የሚሰማበት፣ የተለያዩ አስተሳሰቦች በሰላማዊ ውይይት የሚፎካከሩበት፣ የዜጎች መብትና ደኅንነት የሚከበርበትን ሁኔታ መፍጠር ለዘላቂ መፍትሔ መሠረት ነው።
ከሁሉም በላይ ትግራይ ከሀገራችን ተነጥላ የምትኖር ሳይሆን፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በማኅበራዊ ትስስርና በጋራ የወደፊት ተስፋ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጥብቅ የተሳሰረች ናት። የትግራይ ሕዝብ ችግሮች በብቸኝነት፣ በጥላቻና በተደጋጋሚ ግጭት ሳይሆን፣ በጋራ ጥረት፣ በሰላማዊ ውይይትና በሀገራዊ ትብብር የሚፈቱ ናቸው። አንድነት የልዩነት መጥፋት ሳይሆን፣ ልዩነቶችን አክብሮ በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ የጋራ ጥቅምን ማስጠበቅ ነው።
የሚቀጥለው ትልቅ ተግባር የትግራይን ሕዝብ ከግጭት ወደ ምርታማነት፣ ከመፈናቀል ወደ መልሶ ግንባታ፣ ከተስፋ መቁረጥ ወደ ተስፋ ማሸጋገር ነው። የተቋረጡ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል፣ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ማስፋት፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ማጠናከር፣ የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባትና የተጎዱ ዜጎችን መደገፍ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ሌላ ዙር ጦርነት ሳይሆን ሰላምን፤ ሌላ የፖለቲካ ተስፋ ሳይሆን ተጨባጭ ለውጥን፤ ሌላ የመስዋዕትነት ጥሪ ሳይሆን የኑሮ መሻሻልን ነው። ይህንን ለማሳካት የሕዝቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አመራር፣ ተጠያቂነት፣ ሰላማዊ ተሳትፎና ከሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች ጋር የሚጠናከር ትብብር ያስፈልጋል።
ዘላቂ ድል የሚለካው በጦርነት ሳይሆን በሕዝብ ሕይወት መሻሻል፣ በሰላም መረጋገጥና በልማት ውጤት ነው። የትግራይ ሕዝብ የወደፊት ተስፋ በጋራ ሰላም፣ በሀገራዊ አንድነትና በተጨባጭ ልማት ውስጥ ይገኛል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: