የአንድን የፖለቲካ ድርጅት ሕልውና እና ደኅንነት ከሕዝብ እና ከሀገር ሕልውና ጋር ማቆራኘት መሠረት የሌለው፣ የተዛባ እና አደገኛ አስተሳሰብ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ የፖለቲካ ድርጅት ደኅንነትን ከሕዝብ ደኅንነት ጋር ማስተሳሰር የሕዝቡን ሕልውና በቀጥታ ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ በፍጹም ተቀባይነት የለውም።
ህወሓት ወደ ሃምሳ ገደማ ዓመታትን ያስቆጠረ ድርጅት መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የትግራይ ሕዝብ ግን ለሺህ ዓመታት በጽናት የኖረ እና ወደፊትም የሚኖር ሕዝብ መሆኑን አስረድተዋል።
ህወሓት ከ50 ዓመታት በፊት ያልነበረ እና በአሁኑ ወቅትም ታሪክ እየሆነ ያለ ድርጅት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከትግራይ ወጥቶ ኢትዮጵያን መምራትም አዲስ ነገር አለመሆኑን እና እንደ አፄ ዮሐንስ ያሉ ታላላቅ መሪዎች ከትግራይ ወጥተው ሀገር መምራታቸውን፣ እነርሱ ዛሬ ባይኖሩም የትግራይ ሕዝብ ግን ጸንቶ እንደሚኖር አብራርተዋል።
በመሆኑም ህወሓት እየከሰመ እንደሚሄድ፣ መሪዎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚነሱ እና እንደሚወድቁ፣ መንግሥታትም እንደሚለዋወጡ ጠቅሰው፣ ሕዝብ እና ሀገር ግን ሁልጊዜም ጸንተው እንደሚኖሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
#የመደመርመንግሥት
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: