የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አሸናፊ እና ተሸናፊ በእኩልነት የተስተናገዱበት ታሪካዊ አጋጣሚ እና በሀገራችን አዲስ የሰላም ምዕራፍ የከፈተ ቢሆንም ህወሓት የገባውን ቃል በማጠፉ ስምምነቱ እንዲደናቀፍ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፌዴራል መንግሥት በስምምነቱ መሠረት ተኩስ ከማቆም ጀምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ኃላፊነቱን በአግባቡ ቢወጣም፣ ድርጅቱ ግን ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ወደ መሣሪያ ግዢ እና ወጣቶችን በግዳጅ ወደ መመልመል መግባቱን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ እንዳብራሩት፣ ድርጅቱ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዳይመለሱ በመያዣነት ከመጠቀሙም በላይ የፌዴራል መንግሥት የጀመራቸውን የአየር ትራንስፖርት፣ የባንክ እና የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማስተጓጎል ሕዝቡ ላይ ዳግም ስቃይ አድርሷል ብለዋል።
መንግሥት ‘ጦርነት አያዋጣም፣ ሰላም ይሻለናል’ በሚል ተደጋጋሚ ምክር ቢለግስም፣ ቡድኑ ግን ምክሩን ወደ ጎን በመተው እና ከተለያዩ ኃይሎች ጋር በማበር ወደማያዋጣ ጦርነት መግባቱን ጠቁመዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት በስፋት እየተተገበረ ባለበት ወቅት፣ በትግራይ ግን አንድ ኪሎ ሜትር እንኳ የኮሪደር ልማት አለመከናወኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንጽጽር አቅርበዋል።
ድርጅቱ ለሕዝብ ልማት ከመሥራት ይልቅ፣ ለዕርዳታ የመጣን እህል ከተፈናቃዮች ጉሮሮ እየነጠቀ እና ማዕድናትን እየዘረፈ ድሮኖችን እና የጦር መሣሪያዎችን በመግዛት ላይ ተጠምዶ መቆየቱን አጋልጠዋል።
ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከባድ ድርቅ ተከስቶ እያለ፣ ቡድኑ ጦርነት በማወጅ እና የአየር ትራንስፖርት እንዲዘጋ በማድረግ ሕዝቡን ለከፋ ችግር መዳረጉ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ህወሓት ‘እኔ ከሞትኩ ትግራይ የለችም’ በሚል ከንቱ አስተሳሰብ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖር ቢጥርም፣ የትግራይ ሕዝብ ግን ይህንን መራራ ምዕራፍ አልፎ ወደ ልማት እና ሰላም እንደሚሸጋገር ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።
በበረከት ሽመልስ
#የመደመርመንግሥት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: