Search

ሻዕቢያ ከጥፋት መልዕክተኝነት የማይመለስ ከሆነ መዘዙ እጅግ የከፋ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስጠነቀቁ

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 78

ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ጠላቶች መጠቀሚያ መሆኑን አቁሞ ለቀረበለት የሰላም እና የጋራ ልማት ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ የሚከተለው መዘዝ እጅግ በጣም ከባድ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ የኤርትራው ገዥ ቡድን (ህግደፍ) የራሱን ሀገር እና ሕዝብ የልማት ጥያቄ ወደ ጎን በመተው የቀጣናው የጥፋት ኃይሎች መናኸሪያ እና መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

"የራሱን ችግር ያልፈታ ኃይል ለሌላው ሊተርፍ አይችልም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የውጭ "አይዞህ ባዮች" ጥይት ከማቀበል ባለፈ የራሳቸውንም ችግር መፍታት እንደማይችሉ በመጠቆም፣ ሥርዓቱ ከልማት እና ከትብብር ይልቅ ቀጣናውን የማተራመስ አጀንዳን መምረጡ ፈጽሞ እንደማያዋጣው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።

አገዛዙ በዚያች ሀገር ላይ ያስከተለውን ውድቀት በመጥቀስም፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከመገንጠሏ በፊት በንግድ እና በኢንዱስትሪ ደምቀው የነበሩት ከተሞቿ መደብዘዛቸውን አንሥተዋል።

በአንድ ወቅት ከ300 በላይ ፋብሪካዎች የነበሯትን ኤርትራን ወደ ባዶነት ከቀየረው እና ውቢቷን አስመራን አንሳ እንድትገኝ ካደረገው ሻዕቢያ ጋር መተባበር የጥፋት ጥግ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ አሁንም ለሰላም እና ለጋራ ልማት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ልማትን ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ መሆንን የመረጠው የኤርትራ መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ ታቅቦ የልማት አጋር እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ይሁን እንጂ ሻዕቢያ የውጭ ኃይሎችን ተማምኖ ይህን የሰላም መልዕክት "ጆሮ ዳባ ልበስ" ብሎ በጥፋት መንገዱ የሚገፋበት ከሆነ፣ በመጨረሻ የሚከተለው መዘዝ እጅግ መራራ እና የከፋ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ  አስጠንቅቀዋል።

በበረከት ሽመልስ

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: