ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታዋን ለማፋጠን እና ወጣቶችን የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ ካለመቻቸው ትልልቅ ኢኒሼቲቮች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳቢነት ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት ጋር በትብብር የሚተገበረው የ"ኢትዮ ኮደርስ" ሥልጠና በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆኑ እንደ መሠረታዊ ዳታ ሳይንስ፣ መሠረታዊ ፕሮግራሚንግ፣ መሠረታዊ አርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ እና መሠረታዊ አንድሮይድ ኮትሊን ዴቬሎፐር ያሉ አራት ወሳኝ የቴክኖሎጂ ዘርፎችን ያካተተው ነፃ የኦንላይን ሥልጠና፣ ሀገራችን ወደ ሙሉ ዲጂታላይዜሽን የምታደርገውን ጉዞ የማፋጠን ትልቅ አቅም አለው።
ሥልጠናው ወጣቶች መረጃዎችን የመተንተን፣ ውህድ አርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስን የመተግበር እና ሞባይል መተግበሪያዎችን የመሥራት አቅማቸውን በማጎልበት በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥራ ዕድሎችን እንዲያገኙ መንገድ ከመክፈቱ ባሻገር፣ የራሳቸውን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች (Startups) በመመሥረት ሀገራዊ ችግሮችን በዲጂታል መፍትሔዎች እንዲፈቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የኢትዮጵያ ወጣቶች ክረምታቸው በከንቱ እንዲያልፍ ሊፈቀድ የማይገባ ትልቅ ዕድል መጥቷል” ሲሉ ገልጸው፣ የሚሰጠው የምስክር ወረቀት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው በመሆኑ ሚሊዮኖች ቀድመው የወሰኑበትን ይህን ነፃ ዕድል ወጣቶች እንዲጠቀሙበት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
"ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል መሪ ሐሳብ የተጀመረው የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ውጥን በሦስት ዓመት ለማሳካት የታቀደውን ሥልጠና በሁለት ዓመት በማሳካት፣ አሁን ግቡን ወደ 7 ሚሊዮን ከፍ ማድረግ ተችሏል።
የኮዲንግ እና የሶፍትዌር ልማት መሠረታዊ እውቀቶችን በማስጨበጥ የሰው ኃይል ልማቱን የሚደግፈው ይህ ፕሮግራም፣ የመንግሥት እና የግል ዘርፍ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን የክህሎት መሠረት በመጣል የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዋና ምሰሶ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: