የዲፕሎማሲ ሥራ በአፍሪካ ቀንድ ለሚካሄደው የሰላም ግንባታ ሂደት እጅግ ቁልፍ ስትራቴጂ መሆኑን መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታና ከዲፕሎማሲ ንድፈ-ሐሳቦች ጋር በማዛመድ በጥልቀት የሚተነትነው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር አሰፋ አብዩ አዲስ መጽሐፍ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ፣ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት አመራሮችና አባላት እንዲሁም ምሁራን በተገኙበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ለምረቃ በቅቷል።
ዲፕሎማሲ ለሰላም ግንባታ ስትራቴጂ በአፍሪካ ቀንድ ያለው ተሞክሮና ፈተናዎቹ (Diplomacy As A Peace Building Strategy:-Approaches and challenges in the Horn Africa) በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ በተመረቀበት መርሐ-ግብር ላይ የመጽሐፍ ዳሰሳ ያቀረቡት የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እንደገለጹት፤ የመጽሐፉ ዋነኛ ዓላማ ዲፕሎማሲ ለሰላም ግንባታ ያለውን ፋይዳ አጉልቶ ማሳየት ነው፡፡
ፀሐፊው በዳበረ ሙያዊ ልምድ፣ የአመራርነት ክህሎት፣ በትምህርት ባገኙት እውቀትና ጥልቅ ጥናት ታግዘው ያዘጋጁት መጽሐፍ መሆኑን ከንባባቸው መገንዘባቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ዲፕሎማሲ ከሰላም ግንባታ ባሻገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኀንነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ማሣሪያ መሆኑ በትኩረት እንደተተነተነ ጠቁመዋል፡፡
ዲፕሎማሲያዊ መንገድ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ግጭቶችንና ጦርነቶችን መፍታት ብቻ ሳይሆን፤ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን በመጽሐፉ በሚገባ መብራራቱ የጥንካሬው ማሳያ ነው ብለዋል።
ሌላኛው የመጽሐፍ ዳሰሳ አቅራቢ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም-አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ባዩልኝ ዘመድአገኘሁ በበኩላቸው፤ መጽሐፉ የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታን አጉልቶ ማሳየቱ ጠንካራ ጎኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሰላም ጉዳዮችንና የዲፕሎማሲ ፅንሰ-ሐሳቦችን አስተሳስሮ በማንሳት መፍትሔ እንደሚጠቁም አብራርተዋል።
መጽሐፉ ወቅታዊ የሆኑ አህጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ ክስተቶችና ግጭቶችን በማጣቀስ በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋሉ ችግሮች በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ፖሊሲ አውጪዎች ሃያ አንድ ምክረ-ሐሳቦችን በግብዓትነት ማቅረቡ የይዘት ጥንካሬውን አጉልቶ እንደሚያሳይ ዶክተር ባዩልኝ አመልክተዋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳሰሳ ያቀረቡት አምባሳደር ሽብሩ ማሞ፤ መጽሐፉ ሰላም፣ዲፕሎማሲና ደኀንነት ከድንበር ግጭት ጋር ያላቸውን ትስስር በሚገባ የሚያነሳ መሆኑን ጠቁመው፤ የሀገራችን ዲፕሎማቶች፣ የፀጥታና ደኀንነት አባላት፣ ጥናትና ምርምር ላይ የሚሳተፉ ተማሪዎች በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ግንባታ ጥረቶች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኀንነት አማካሪ ዶ/ር ቀነአ ያደታ በበኩላቸው፤ መጽሐፉ ወሳኝ የሆኑ የሰላም፣ ግጭትና ዲፕሎማሲ ጽንሰ-ሐሳቦችን በሚገባ እንዳነሳ ጠቅሰዋል፡፡
በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት የሚታዩ የድንበር ወሰን ችግሮች የፀጥታና ደኅንነት ስጋት እንደሚፈጥሩ በመግለጽ፤ መጽሐፉ ለባለድርሻ አካለት ግብዓት እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ድንበሮች ጥናት ግብረ-ኃይል አስተባባሪ አምባሳደር ኢብራሂም አድሪስ በበኩላቸው፤ መጽሐፉ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ክፍተት በሆኑት የድንበር ግጭት ፣ ሰላምና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መሆኑ ጠቅሰው፤ በዲፕሎማሲ ፣ፀጥታና ደኀንነት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎችና አመራሮች ጠቃሚ ግብዓቶችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል። በቀጣይ በዲፕሎማሲና የሰላም ግንባታ ዘርፎች የካበተ ሥራ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎችም መጽሐፍ ለመጻፍ እንዲነሳሱ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አሰፋ አብዩ በፀጥታና ደኅንነት ተቋማት እንዲሁም በዲፕሎማሲ የተልዕኮ ሥምሪት ያገኙት ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም የፒኤችዲ ድግሪ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ያዘጋጁት ጥናታዊ ጽሑፍ መጽሐፉን ለማዘጋጀት መነሻ እንደሆናቸው ጠቁመው፤ ከዝግጅት እስከ ሕትመት ባለው ሂደት ተሳትፎ ላደረጉት አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም ዶ/ር አሰፋ ከመጽሐፉ ሽያጭ ከሚገኝ ገቢ 100ሺ ብር ለሀገራችን ሰላምና ደኅንነት መስዕዋትነት ለሚከፍለው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም 100ሺ ብር ደግሞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በስምሪት ላይ እያሉ ጉዳት ለደረሰባቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሚያበረክቱ በመድረኩ አስታውቀዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: