Search

ኢትዮጵያ እና ጆርዳን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ከፈቱ

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 65

ኢትዮጵያና ጆርዳን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ሽግግር፣ በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና በልምድ ልውውጥ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ የጆርዳን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና በአፍሪካ ኅብረት የጆርዳን ቋሚ መልዕክተኛ አምጃድ አል ሞውማኒ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን የጎበኙ ሲሆን፣ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) አቀባበል በማድረግ የተቋሙን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና ለአገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ልማት እያበረከተ ያለውን የላቀ አስተዋጽኦ በዝርዝር አስረድተዋቸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት የኢንስቲትዩቱ ቁልፍ ሥራዎች የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ፣ የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታትና ሀገራዊ የዲጂታል ሽግግሩን በማፋጠን ላይ ያተኮሩ ናቸው።

አምባሳደር አምጃድ አል ሞውማኒ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በዲጂታል ሽግግር መስኮች የሰነቀችው ራዕይና እያስመዘገበች ያለው ፈጣን እድገት እጅግ አበረታች መሆኑን ገልጸው፣ የተቋሙ ተግባራት በፈጠራ ላይ የተመሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ከተያዘው ሀገራዊ ራዕይ ጋር አብረው የሚራመዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጆርዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት ከማጠናከር ባሻገር፣ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መስኮችና በአቅም ግንባታ ዘርፎች ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: