በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ሥራዎች እና በተለይም በከተማዋ እምብርት የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ ታሪካዊ እና ለትውልድ የሚሻገሩ መሆናቸውን ከአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች መሰከሩ።
እነዚህ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ሲካሄድ በነበረው የአፍሪካ የሕክምና ተቋማት ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ የመጡ ሲሆን፣ በቆይታቸውም የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ የተለያዩ ዘመናዊ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ኢትዮጵያ የበርካታ ደማቅ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን በኩራት ገልጸው፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነው ታላቁ የአድዋ ድል ደግሞ ዋነኛው መለያዋ መሆኑን አብራርተዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ አክለውም፣ ይህ ግዙፍ የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያን ጥልቅ ታሪክ በውል የሚገልጽ እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ ሕያው ሆኖ የሚሻገር መሆኑን በመጥቀስ ለታሪካዊነቱና ለሥነ-ሕንፃው ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በስኬት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የሕክምና ተቋማት (Mededafrica 2026) ኮንፈረንስ በይፋ ተጠናቋል።
የዘንድሮውን ታሪካዊ መድረክ ኢትዮጵያ በብቃት ያስተናገደች ሲሆን፣ ቀጣዩን የአፍሪካ የሕክምና ተቋማት (Mededafrica 2027) ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ ደግሞ ናሚቢያ ኃላፊነቱን በይፋ ተረክባለች።
በመሃሪ ዓለሙ