Search

የፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ፤ ከትላንት የነፃነት ፅናት እስከ ዛሬው የመደመር ራዕይ

ረቡዕ ነሐሴ 13, 2018 137

አፍሪካ፣ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገችና የሰው ልጅ መገኛ የሆነች ታላቅ አህጉር ብትሆንም፣ 1884 . በተካሄደው የበርሊን ጉባኤ (Scramble for Africa) በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች እንደ ሸቀጥ ተከፋፍላ የጨለማና የመከራ ዘመን ውስጥ እንድታልፍ ተፈርዶባት ነበር።

ይህ ታሪካዊ ግፍ አህጉሪቱን በድንበር፣ በቋንቋና በባህል ከፋፍሎ ለረጅም ዘመናት ለብዝበዛ ዳርጓታል።

ነገር ግን ይህን የጨለማ ጊዜ ያስወገደው፣ የጥቁር ሕዝቦችን የነፃነት ተስፋ ያበራውና የፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ እንዲጸነስ ያስቻለው ታሪካዊው ክስተት የኢትዮጵያ የዓድዋ ድል ነው።

ዓድዋ፣ አፍሪካውያን በባርነት ቀንበር ሥር ሆነው ለነፃነት የሚታገሉበትን መንፈሳዊ ጉልበት የፈጠረ የፅናት ምልክት ነው።

ዊሊያም ሄንሪ፣ ቤኒቶ ሲልቪያን እና ማርከስ ጋርቬይን የመሳሰሉ ጥቁር የነፃነት ታጋዮች ኢትዮጵያን እንደ ነፃነት ተምሳሌት አድርገው ተመልክተዋታል።

ማልኮም ኤክስ "ኢትዮጵያ የጥቁርን ቀጣይ ዕድገት ያስመሰከረች የምድርን ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረች ሀገር ናት" ማለቱ የዚህን ሥነ-ልቦናዊ ልዕልና ጥልቀት ያሳያል።

የጋናው ክዋሜ ንክሩማ፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ እና የሴኔጋሉ ሊኦፖልድ ሴንጎር የመሳሰሉ የነፃነት አባቶችም ይህንን የዓድዋን እና የፓን-አፍሪካኒዝምን መንፈስ በመሰነቅ ነበር አፍሪካን ነፃ ለማውጣት የታገሉት።

1955 . (... ግንቦት 25 ቀን 1963) የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት፣ የካዛብላንካ እና የሞኖሮቪያ ቡድኖች የነበራቸውን የሐሳብ ልዩነት በማስታረቅ ረገድ፣ ኢትዮጵያ በአፄ ኃይለ ሥላሴ እና በዲፕሎማቱ አቶ ከተማ ይፍሩ አማካኝነት የተጫወተችው ሚና አህጉሪቱን ከመበተን ያዳነ ታላቅ የአብሮነት አሻራ ነው። 

ከዚያም ወዲህ፣ ድርጅቱ (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) በርካታ ሀገራትን ከቅኝ ግዛት ነፃ ከማውጣት ጀምሮ፣ የአፓርታይድን ሥርዓት በማስወገድ እና አህጉራዊ ሰላምን በማስከበር በኩል ጉልህ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ይሁንና፣ ዛሬም አፍሪካ ፈተናዎች አልተለይዋትም። የውጭ ጣልቃ ገብነት (ኒዮ-ኮሎኒያሊዝም) በብድርና በእርዳታ ስም የሚደረግ የኢኮኖሚ ጥገኝነት፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ እንዲሁም አምባገነንነት አሁንም የአህጉሪቱን ብልፅግና እያደናቀፉ ይገኛሉ። እነዚህን ዘመናዊ ፈተናዎች ለማለፍ የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ በአዲስ መልክ መተርጎም እና በተግባር መታየት ግድ ይለዋል።

በዚህ ዘመን የፓን-አፍሪካኒዝምን እሳቤ በተግባር ከሚያሳዩት ታላላቅ መሪዎች መካከል የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ፣ "መደመር" በሚለው ዕሳቤ፣ አፍሪካውያን ከጥላቻ፣ ከመከፋፈልና ከውጭ ጥገኝነት ወጥተው በጋራ ማደግ እንዳለባቸው በተግባር እያሳዩ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማጠንጠኛ የሆነው "ጎረቤትን ያስቀደመ ዲፕሎማሲ" የዘመናዊው ፓን-አፍሪካኒዝም ሕያው ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ በሱዳን የፖለቲካ ቀውስ፣ በሶማሊያ ሰላም ማስከበር፣ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስምምነት ዙሪያ የተጫወተችው አዎንታዊና የማስታረቅ ሚና፣ "የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፈታት አለባቸው" የሚለውን የፓን-አፍሪካኒዝም መርህ ያረጋገጠ ነው።

ከዚህም ባሻገር፣ በመደመር ፍልስፍና የተመራው የኢትዮጵያ ቀጠናዊ ውህደት ራዕይ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን (በመንገድ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በባቡር መስመር እና በወደብ አጠቃቀም) መሠረት ያደረገ ነው።

ይህ አካሄድ ከእርስ በርስ ግጭትና ከውጭ ኃይሎች የውክልና ጦርነት ወጥተን፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን አስተባብረን አፍሪካን የዓለም የኢኮኖሚ ማዕከል ማድረግ እንችላለን የሚል ፅኑ እምነትን ያዘለ ነው።

በአጠቃላይ፣ ዛሬ ላይ 1.4 ቢሊዮን ሕዝብ ያላትን አፍሪካ የውጭ ኃይሎች የጂኦ-ፖለቲካዊ መጫወቻ ከመሆን አድነን፣ በመደመር እና በአንድነት ማበልፀግ ይኖርብናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) እንዳስመሰከሩት፣ የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ያለው በእጃችን ነው፤ "አጀንዳ 2063" ራዕይም ዕውን የሚሆነው ኢትዮጵያ የጀመረችውን ጎረቤትን ያስቀደመና በፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ የታነፀውን የጋራ ብልፅግና መንገድ አፍሪካውያን ሁሉ ሲከተሉት ብቻ ነው!

በአዶኒያስ /አረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: