Search

ከወረቀት ወደ ዲጂታል የተሸጋገረው ዘመናዊ አገልግሎት

እሑድ ኅዳር 28, 2018 15

አዲስ አበባ ላለፉት 14 ዓመታት ስትጠቀምበት የነበረው የነዋሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለብልሹ አሰራር በር ሲከፍት እና የከተማዋን ዘመናዊነት ሲፈታተን ቆይቷል።
አሁን ግን በኢትዮጵያ የከተማ አስተዳደር ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ተጀምሯል። አዲስ አበባ ከወረቀት ክምር እና ከተንዛዛ ቢሮክራሲ ተላቃ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ወደ ታገዘ ዘመናዊ አሰራር ተሸጋግራለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የለማ የተቀናጀ የሲቪል ምዝገባ ስርዓት ይፋ አድርጓል።
ይህ አዲስ ስርዓት፤ ከተማዋን ወደ "ስሉጥ ከተማ" (Smart City) ለመቀየር የሚደረገው ጉዞ ወሳኝ አካል ተደርጎ ተወስዷል።
ይህ ለውጥ የቴክኖሎጂ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የከተማዋ ነዋሪዎች ሳይንገላቱ፣ በቤታቸው ሆነው ጉዳያቸውን የሚያስፈጽሙበት፣ ፍትሐዊነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሥርዓት የመገንባት ጥያቄ ነው።
አዲሱ አሰራር ተገልጋዮች ለእንግልት እንዳይዳረጉ እና ለብልሹ አሰራር እንዳይጋለጡ በማድረግ ረገድ እንደ ትልቅ መፍትሄ የሚታይ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩም አስታውቋል።
የዚህ ፕሮጀክት ማጠንጠኛ የሆነው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፤ ስርዓቱ በቀላሉ መረጃዎችን እንዲያደራጅ ብቻ ሳይሆን፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቀላሉ እንዲግባባ ያስችለዋል።
አዲሱ መተግበሪያ ከጤና፣ ከኢሚግሬሽን፣ ከፍርድ ቤቶች፣ ከብሔራዊ መታወቂያና ከመሳሰሉት ተቋማት ጋር ያለችግር ይናበባል።
ይህ ማለት አንድ ነዋሪ አገልግሎት ለማግኘት ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላው ወረቀት ይዞ የሚዞርበትን አድካሚ መንገድ ያስቀራል።
በሌላ በኩል፣ ይህ ዲጂታል ሽግግር ለወንጀል መከላከል ሥራ ትልቅ እፎይታን ይዞ መጥቷል።
ቴክኖሎጂው ተመሳስለው የሚሰሩ ሐሰተኛ ሰነዶችን በመለየት ረገድ ፍቱን መድኃኒትም ነው።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንሱ ትክክለኛውን ሰነድ ከሐሰተኛው የመለየት ብቃት ስላለው፣ በዘርፉ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ አሰራር ከመሰረቱ ለመናድ ያስችላል።
ቴክኖሎጂውን ውጤታማ ለማድረግ የሰው ኃይሉን በስልጠና የማብቃት እና የማደራጀት ስራዎች እንደ ትልቅ ቅድመ ሁኔታ መሠራቱንም የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) አስረድተዋል።
ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ በ50 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው ይህ ሥርዓት፤ የከተማዋን የአገልግሎት አሰጣጥ ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ ቴክኖሎጂን ለሰው ልጆች ምቾት እና ለፍትሐዊ አሰራር እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማሳያ ይሆናል።
 
በመሀመድ ፊጣሞ