በቴክኖሎጂ የተደገፉ የአገልግሎት ዘርፎችን በተለመደው መንገድ ከመሥራት ባለፈ ማስፋት፣ ምርታማነትን ማሳደግ እና ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማምጣትን መልመድ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት አዲስ የተገነባውን ዲጂታል "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሲስተምን እና ተያያዥ የሪፎርም ሥራዎችን አስመልክተው ለሲቪል ሰርቪስ መመሪያና አደራ በሰጡበት ወቅት ነው።
በንግግራቸውም የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የዚሁ ስኬታማ አሠራር አርዓያ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተቋሙ ቁሳቁሶችን ገዝቶ ከመደርደርና ሕንፃዎችን ብቻ ከማነጽ ባለፈ ያመረታቸውን የፈጠራ ውጤቶችና አገልግሎቶች ወደ ገቢ በመቀየር ረገድ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
አንድ ተቋም ሥራን ሠራሁ ማለት የሚችለው ያቀረበው ሪፖርትና የሥራ ውጤት በተግባር ገቢ ማምጣት ሲችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ ሠርተው ተቋማዊ ገቢ ካላስገኙ እና ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ካላበረከቱ የተገኘው ስኬትና ደስታ ሙሉ ሊሆን እንደማይችል አስገንዝበዋል።