Search

በአዲስ አበባ ጤናማ የኪራይ ቤት አቅርቦት እንዲኖር በርካታ አስተዳደራዊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው:- የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 67

በአዲስ አበባ ከተማ ጤናማ የኪራይ ቤት አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል፣ የአከራይና ተከራይ ውል ምዝገባን ጨምሮ በርካታ አስተዳደራዊ ስራዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው ይህንን ያስታወቀው ዓመታዊ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መወሰኛ ጥናት ላይ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት መድረክ ላይ ነው።

በዚሁ ምክክር ላይ በቤት ኪራይ ተመን ላይ ያተኮረ ጥናት የቀረበ ሲሆን፣ ከመኖሪያ ቤት ተከራዮች፣ አከራዮችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

ለ2019 በጀት ዓመት የተዘጋጀው የገበያ ዋጋ ጥናት ወደ ተግባር ከመሸጋገሩ በፊት፣ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ እንዲህ ያሉ የምክክር መድረኮች መዘጋጀታው ተገልጿል።

ይህ ጥናት በግል የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ዋጋ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን፣ የዓመታዊ ማስተካከያዎችን አስፈላጊነት እና ተገቢውን የዋጋ መጠን በተመለከተ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን  ያካተተ ነው።

ጥናቱ በዋናነት አከራዮች ፍትሃዊ ገቢ እንዲያገኙ የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተከራዮች ከአቅማቸውና ከገቢያቸው ጋር የተመጣጠነ የኪራይ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስችል ምህዳር መፍጠርን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

በመቅደስ እንዳለ