ሀገራችን በማያቋርጥ የዕድገት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ በየጊዜው የሚወጡ የዓለም አቀፍ ተቋማት መረጃዎች ያመላክታሉ።
የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በፈረንጆቹ 2026 ኢትዮጵያ የ9 ነጥብ 2 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ባወጣው የትንበያ ሪፖርት መግለጹ የሚታወስ ነው።
ይህም ኢትዮጵያን በሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት በፈጣን ዕድገቷ ቀዳሚዋ ሀገር ያደርጋታል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ትንበያ በመሻገር በዘንድሮው በጀት ዓመት በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ ጫና ጭምር በመቋቋም የ10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ታስመዘግባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ በቅርቡ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል።
ሀገራት በተፈጥሮ ጸጋዎቻቸው አጠቃቀም ላይ ተመስርተው በፍጥነት ወደ ትልቅ የኢኮኖሚ ባለቤትነት ሊሸጋገሩ ይችላሉ። ሆኖም አንዲት ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው የሚባለው መሰረታዊና መዋቅራዊ የሆነ የኢኮኖሚ ሽግግር ማምጣት ስትችል መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው።
ለአብነትም በአንድ ወቅት በከፍተኛ የዕዳ ማጥ ውስጥ ተዘፍቀው የነበሩ እንደ ሲንጋፖር፣ ታይዋን፣ ሆንግ ኮንግ እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት "የታይገር ኢኮኖሚ" የሚያሰኛቸውን ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ መዋቅራዊ ሽግግር አድርገዋል።
እነዚህ ሀገራት በጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ የዓለምን የኢኮኖሚ ታሪክ በአዲስ መልክ የጻፉ ሲሆን፣ ዛሬም ይህን መሰል የታሪክ ምዕራፍ በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ እየተደገመ ይገኛል።


ኢትዮጵያ ከዕዳ ወደ ምንዳ፣ ከተስፋ መቁረጥ ወደ ካፒታል ገበያ ንቅናቄ በመሸጋገር ላይ ትገኛለች። ሀገራችን ታስመዘግባለች ተብሎ የሚጠበቀው የኢኮኖሚ ዕድገት በማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም በተወሰደው ደፋር፣ ፈጣን እና ጥብቅ የፖሊሲ እርምጃዎች መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ከእነዚህም እርምጃዎች መካከል የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ተመስርቶ እንዲወሰን መደረጉ የወጪ ንግድ እና የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲያንሰራራ አድርጎታል።
በገንዘብ ፖሊሲ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮችን የብድር ገደብ በማጥበቅ እና የ15 በመቶ ዋና የወለድ ተመንን ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም ከመንግሥታት አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር በተደረገ ስምምነት የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ክፍያ እንዲራዘም መደረጉ፣ ለልማት ፕሮጀክቶች ትልቅ የፊስካል አቅም ፈጥሯል።
ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ፣ ከዲጂታል ኢኮኖሚ እስከ ካፒታል ገበያ ድረስ ያለው ፈጣን ንቅናቄ ሀገራችን የጀመረችው የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጉዞ የማይቀለበስ መሆኑን ያሳያል።
ስለሆነም የ10 ነጥብ 2 በመቶ ሀገራዊ ዕድገት ትንበያ የቁጥሮች ድምር ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር የተረጋገጠ የእመርታችን ማሳያ እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጽኑ መሠረት ላይ ማረፉን ማረጋገጫም ጭምር ነው።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ