Search

በእውቀት ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲና የጋራ ልማት፡- የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ቀጣናዊ ተፈላጊነቷን ለማሳደግ እየተካሄደ ያለው ስኬታማ የደኅንነት ጉዞ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 64

በቀጣናውና በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ ከፍ እያለ የመጣው ኢትዮጵያ፥ የውጭ ዲፕሎማሲዋንና ብሔራዊ ጥቅሟን ይበልጥ ለማስከበር በምን ዓይነት ስትራቴጂካዊ መንገድ ላይ ትገኛለች?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ “አሁናዊ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነት ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች” በሚል መሪ ቃል ባካሄደው ዓመታዊ የደህንነት የምክክር ጉባዔ ላይ፥ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በእውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተመላክቷል።

በጉባዔው ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በሀገር ውስጥ ያለ የትኛውም ችግር ሀገረ መንግስቱን መገዳደር የሚችል አለመሆኑን በፅኑ አስምረውበታል።

ስለሆነም ኢትዮጵያ ያላትን ቀጣናዊ ትስስር አስቀድሞ በመተንተንና በመረጃ ላይ በተመሰረተ መልክ በመምራት ብሔራዊ ጥቅሟን የማስከበር ስኬታማ ጉዞዋን አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባ ገልፀዋል።

ሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሟንና የደህንነት ቀለበቷን ለማስጠበቅ በምታደርገው በዚህ ስኬታማ ጉዞ ላይ የባህር ኃይል ሚናው የጎላ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚኖር ግንኙነት “ገቢር ነበብ” (Proactive) ስትራቴጂን መከተል እንደሚገባና ተቋማቸው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የባህር ኃይል ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት እያጠናከረ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን የሚፈልጉ የውጭና የውስጥ ኃይሎችን ለመመከት የውስጥ ጥንካሬን ማጎልበት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ሀገራችን የአካባቢውን ሀገራትና ሕዝቦች በልማትና በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠች መሆኗ በቀጣናው ያላትን ተፈላጊነትና መሪነት ይበልጥ እያሳደገው መጥቷል ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ አያይዘውም የኤርትራ መሪ ለሥልጣኑ ማቆያነት በኢትዮጵያ ላይ ትርምስ ለመፍጠር ቋሚ አጀንዳ አድርጎ ቢይዝም ፍላጎቱ የማይሳካ መሆኑን ገልጸው፤ በተመሳሳይ ከሥልጣን ውጪ መኖር የማይችለው የቀድሞው ሕወሃት ጽንፈኛ ቡድንም የትግራይን ሕዝብ ሳይሆን የራሱን የሥልጣን ጥም ለማርካት የሚተጋ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የትግራይን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥና ተስፋውን የሚያለመልሙ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የውስጥ አንድነቷን በማጠናከርና ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ልማት ላይ በመሠረተችው ብልህ ዲፕሎማሲ አማካኝነት የብሔራዊ ደህንነት ተግዳሮቶቿን በብቃት እየመከተች ወደ ላቀ ከፍታ እየተጓዘች መሆኑን መላው ሕብረተሰብ ሊገነዘበው ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።