ኢትዮጵያ የዳታ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችላትን ግዙፍ ብሔራዊ የዳታ ክላውድ በመገንባት ላይ እንደምትገኝ እና በጥቂት ዓመታት ውስጥ ላፕቶፕና አይፓድ ማምረት የሚያስችል የሃርድዌር ፋብሪካ እያቋቋመች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት አሁን በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እየተገነባ ያለው ብሔራዊ ክላውድ በየተቋማቱ ያሉ የዳታ ሴንተሮችን አቅም በግማሽ የሚበልጥ እጅግ ግዙፍ አቅም ያለው ነው።
ይህ መሰረተ ልማት የሀገራችንን ምስጢራዊ መረጃ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
ከሶፍትዌር እና ዳታ ጥበቃ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ወደ ሃርድዌር ምርት መሸጋገሯን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤአይ ኢንስቲትዩት ከአንዳንድ ተቋማት እና ከኤአይ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የላፕቶፕ እና የአይፓድ ፋብሪካ ደምሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ይህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ልጆች ወደ ሙሉ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት የሚያሸጋግር ታሪካዊ መሰረት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ 55 ሚሊዮን የቴሌብር እና 45 ሚሊዮን የዲጂታል አይዲ (ፋይዳ) ተጠቃሚዎችን ማፍራቷም በዲጂታል ዘርፍ የተመዘገበ ትልቅ ስኬት መሆኑ ተጠቅሷል።