ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የነበራትን የጥገኝነት ምዕራፍ በታሪክ ሰነድነት በማስቀመጥ በአፍሪካ ደረጃ አዲስ የፈጠራ ምዕራፍ ከፍታለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተጀመረው ‘ዲጂታል ለልህቀት’ ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ቴክኖሎጂ አመንጪነት መሸጋገሯን በተግባር ያረጋገጠ እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በዘላቂነት ለማምረት የተዘረጋው የስትራቴጂያዊ ማዕቀፍ መገለጫ ነው።
በጉባኤው በይፋ የተመረቀው በአፍሪካ ቀዳሚው የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ የተለያዩ ተቋማትን አገልግሎት በአንድ መድረክ በማምጣት የቢሮክራሲ ሂደትን የሚያቀል ነው።

ይህን መተግበሪያ ጨምሮ እንደ መሶብ ያሉ በሀገር በቀል ዕውቀት የተደራጁ ዲጂታል መድረኮች፣ የዜጎችን የዕለት ተለት ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች በዘመናዊ መረብ የሚያስተሳስሩ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው።
በዚህ መልኩ አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ ማቅረብ የዜጎችን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጪ በመቆጠብ የሀገርን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
ቴክኖሎጂ ለልማት ሥራዎች ሲውል፣ ለሀገር ውስጥ አቅም ግንባታ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። አገልግሎቶች በአንድ መድረክ ሲሰባሰቡ ለምርታማነት ዕድገት፣ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እና ለዘመናዊ የንግድ አሠራር መሠረት ይጥላሉ።

የዲጂታል ሽግግር አሠራሮችን ግልጽ እና ቀልጣፋ በማድረግ በዘመናዊው ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን የሚደረገውን ጥረት ያፋጥነዋል።
አዲሱ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ ለነገው ዲጂታል ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆን ዲጂታል የንግድ ልውውጥን ከማዘመን፣ መሠረታዊ አገልግሎት እስከ መስጠት ባለው ሰንሰለት ውስጥ የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው።
በሃና ምንዳሁን