አሜሪካ እና ኢራን የሚያደርጉትን ድርድር በአውሮፓዊቷ ስዊዘርላንድ በዛሬው ዕለት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት በድርድሩ ላይ ለመካፈል ወደ ስዊዘርላንድ መግባታቸው ተገልጿል።

በዚህም ከአሜሪካ በኩል ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ እንዲሁም የኢራን ልዑካን ቡድን አባላት የሆኑት የፓርላማው አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራጋቺ ስዊዘርላንድ መድረሳቸው ተመላክቷል።

ዛሬ ይጀመራል በተባለው የመጀመርያው ዙር ንግግር ጄዲ ቫንስ በኒውክሌር ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሁም በሊባኖስ የተኩስ አቁም ላይ መግባባት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።
እስራኤል እና ሊባኖስ ሰላማቸው እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ያለማቋረጥ መነጋገር ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም የንግግሩ ዓላማ እና ቀጣናውን ሰላማዊ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ማድረግ ነው ብለዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ሀገራቸው ተደራዳሪው ወገን ግዴታውን ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እንደምትፈልግ አመልክተዋል።
በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ከዚህ በፊት የተካሄዱ ውይይቶችን ስታስተናግድ እና ስታሸማግል የቆየችው ፓኪስታን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ሼህባዝ ሻሪፍ በንግግሩ ላይ እንደምትሳተፍ ቢቢሲ ዘግቧል።
በያዝነው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢራኑ አቻቸው መሱድ ፔዜሽኪያን ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል 14 ነጥቦችን የያዘ የመግባቢያ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ወዲያውኑ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር እና ተጨማሪ ድርድር በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ እንደሚደረግ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።
የስምምነቱ እንቅፋት የሆነው በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት መሆኑም ተመላክቷል።
አሜሪካ እና ኢራን መስማማታቸውን ይፋ ካደረጉ ጊዜ ጀምሮ ሄዝቦላህ እና እስራኤል አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።