Search

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ57ኛ መደበኛ ስብሰባው ያሳለፋቸው 5 ዋና ዋና ውሳኔዎች

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 88

ምክር ቤቱ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ የኢኮኖሚ፣ የልማትና የፖሊሲ ማሻሻያ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ሙሉ በሙሉ ያጸደቃቸው ዋና ዋና ውሳኔዎች በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርበዋል፦

1. የ637.5 ሚሊዮን SDR የብድር ስምምነቶች ማፅደቅ

ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማኅበር (IDA) ጋር የተፈረሙና ለሦስት ታላላቅ ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ የብድር ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አስተላልፏል።

ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማስፈጸሚያ፦ 437.4 ሚሊዮን SDR

ማኅበረሰብ ተኮር የመሬት አያያዝ፦ 145.5 ሚሊዮን SDR

የአየር ንብረት የማይበገር የመስኖ ልማት፦ 54.6 ሚሊዮን SDR

2. የአገልግሎት ክፍያ መወሰኛ ረቂቅ ደንቦች ማፅደቅ

የሦስት የመንግሥት ተቋማት የውስጥ ገቢ አቅምን ለማሳደግና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የቀረቡ ረቂቅ ደንቦችን ግብዓት በማከል በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

ባለድርሻ ተቋማት፦ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፣ እና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት።

3. የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (NDB) አባልነት ስምምነት

ኢትዮጵያ ባንኩን በአባልነት እንድትቀላቀልና ለሀገራዊ መሠረተ ልማትና ማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት አማራጭ የገንዘብ ምንጭ እንድታገኝ የተዘጋጀውን የአባልነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።

4. አዲሱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ

የዘርፉን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ ከዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ዕድገትና ከተሞች መስፋፋት ጋር ለማጣጣም የቀረበውን አዲስ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ መርምሮ ከዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

5. አዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲ

ላፉት 20 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የነባሩን ፖሊሲ ክፍተቶች ለማረም፣ በከተሞች የታዩ አበረታች የሪፎርም ለውጦችን ለማጽናትና የከተማ-ገጠር ትስስርን ለማጠናከር በአዲስ መልክ የተዘጋጀውን የከተማ ልማት ፖሊሲ ከዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።