በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ታሪካዊ የሰላም ስምምነት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር አምባሳደር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ በታላቅ ደስታ የተቀበሉት ሲሆን፤ ስምምነቱ ግጭቶችን ለማስቆም፣ ቀጠናዊ ውጥረትን ለማርገብና በመካከለኛው ምስራቅ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የተነሳ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ ይህንን ዲፕሎማሲያዊ እመርታ በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፤ የተደረሰው ስምምነት ግጭቶችን ለመፍታት እና በሀገራት መካከል እምነትን ለመገንባት የውይይት እና የዲፕሎማሲ ያለውን የላቀ ኃይል በተግባር ያሳየ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አክለውም ደኅንነቱና ብልጽግናው ለመላው ዓለም ከፍተኛ ፋይዳ ባለው በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና፣ የጋራ ትብብርንና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ስምምነቱ አዲስ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን አስታውቀዋል።
አምባሳደር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ለሂደቱ መሳካት የተሳተፉትን አካላት ገንቢ ሚና ያደነቁ ሲሆን፣ በተለይም ለስምምነቱ በስኬት መቋጨት አስተዋጽኦ ላደረጉት ጥረቶች ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ ዕውቅና ሰጥተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተደራዳሪ ወገኖች መካከል ውይይት እንዲቀጥልና መተማመን እንዲፈጠር የሽምግልና እንዲሁም የማመቻቸት ሚና የተጫወቱትን የፓኪስታን ኢስላማዊ ሪፐብሊክን፣ የኦማን ሱልጣኔትን እና የኳታር መንግሥትን የላቀ አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
ይህ ስምምነት አለመግባባቶችን በውይይትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በሰላም ለመፍታት ከሚሠራው ከአፍሪካ ኅብረት ጽኑ መሠረታዊ መርህ ጋር ፍጹም የተጣጣመ መሆኑን ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።
ለዘላቂ ሰላም፣ ለቀጠናዊ መረጋጋት እና ለተጠናከረ ዓለም አቀፍ ትብብር መንገድ ይከፍታል የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ ኅብረቱ በሀገራት መካከል ሰላምን፣ ትብብርንና እርስ በርስ መከባበርን የሚያጎለብቱ ማናቸውንም ተነሳሽነቶች ለመደገፍ ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል።