Search

የኢጋድ አባል ሀገራት የሳይበር ድሪል በአዲስ አበባ ተጀመረ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 76

በምሥራቅ አፍሪካ የሳይበር ደኅንነት አቅምን ለማሳደግና ድንበር ተሻጋሪ የሳይበር ጥቃቶችን በጋራ ለመከላከል ያለመው የኢጋድ አባል ሀገራት የሳይበር ድሪል (IGAD Regional Cyber Drill 2026) በአዲስ አበባ በይፋ ተጀምሯል።

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የዲጂታል ትስስር ፕሮጀክት ሥር የተዘጋጀውና ለአምስት ቀናት የሚቆየው ይህ "ቀጠናዊ የሳይበር ደኅንነት ልምምድ" ዛሬ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና መሥሪያ ቤት ተጀምሯል።

መድረኩ ከኢጋድ አባል ሀገራት የተውጣጡ የሳይበር ደኅንነት ተቋማት፣ የሕግ አስከባሪ አካላት እና የቁልፍ መሠረተ-ልማት ተቋማት አመራሮችን በአንድ ላይ ያሰባሰበ ትልቅ መድረክ ነው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ "ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት" የሚለውን ኢትዮጵያዊ ብሂል በማንሳት፣ የሳይበር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ መሥራት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋነኛ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም "ትናንት በነበርንበት ሆነን የዛሬን እና የነገን ፈተናዎች መጋፈጥ አንችልም፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የቀጠናዊ ትስስራችን መሠረት እየሆኑ በመጡበት በአሁኑ ወቅት የዲጂታል መሠረተ ልማቶቻችንን ደኅንነት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኢጋድ ተወካይ አቶ አበበ ቢሆኝ በበኩላቸው፣ የሳይበር ጥቃቶች ድንበር እንደማይገድባቸው ጠቅሰው፣ በአንድ ሀገር ላይ የሚደርስ ጥቃት በቀጠናው ላይ ፈጣን ተፅዕኖ ስለሚያሳድር በጋራ መቆምና የተቀናጀ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ይህ ለአምስት ቀናት የሚቆየው ፕሮግራም በዋናነት በፖሊሲና ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር፣ ስጋቶችን በመለየትና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ዙሪያ የቴክኒክ አቅምን መገንባት ላይ ያተኩራል።

በተጨማሪም በቴሌኮም፣ በፋይናንስና በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን የመከላከል ሀገራዊ ልማድ እንዲሁም የራንሰምዌር ጥቃቶችንና የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻዎችን በጋራ የመከላከል ቀጠናዊ የሳይበር ደኅንነት ልምምዶችን ያካተተ ነው።

በዓለም ባንክ፣ በአለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (ITU)፣ በሳይበር ሬንጅስ (Cyber Ranges) እና በማክሚላን አማካሪነት ድጋፍ የሚካሄደው ይህ ልምምድ ሲጠናቀቅ፤ በቀጠናው ያሉ ክፍተቶችን በትክክል በመለየት ወደፊት ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን በጋራ ለመመከት የሚያስችሉ ተግባራዊ መፍትሔዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።