Search

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና አፍሪካ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 86

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (ዩኤኤ) ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላቸውን የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንት እና የጂኦፖለቲካዊ ትስስር ይበልጥ ለማሳደግ ያለመው "ሂሊ ዲያሎግ - አፍሪካ ኤዲሽን" (Hili Dialogue Africa Edition) የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት (IFA) ከአንዋር ጋርጋሽ የዲፕሎማሲ አካዳሚ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ፤ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች እና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል።

ይህ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ዲፕሎማቶችን፣ የፖሊሲ አጥኚዎችንና የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ያሳተፈ መድረክ፤ በኤምሬቶችና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ዘመኑን የዋጀ መስተጋብር ማጎልበት ዋነኛ አጀንዳው አድርጓል።

ውይይቱ በተለይም በአህጉሪቱ እየታየ ላለው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ሽግግር እና በቀጣናዊ የባሕር በሮች አካባቢ ለሚስተዋለው ስትራቴጂካዊ ፉክክር ምላሽ የሚሆኑ የፖሊሲ አማራጮችን ለማመላከት ያለመ ነው። በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው፤ ንግድና ኢንቨስትመንት የሁለቱ ወገኖች አጋርነት ዋነኛ ምሰሶዎች ሆነው ይቀጥላሉ።

ከዚህ ባለፈም ትብብሩ እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ ታዳሽ ኃይል እና የላቁ የዲጂታል መሠረተ-ልማት ግንባታዎች ላይ በማተኮር፤ የአፍሪካ ሀገራትን ወደ ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት (Global Value Chain) ለማስገባት በትኩረት እንደሚሰራ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ለዚህ ቀጣናዊ ዲፕሎማሲ ስኬት እንደ ዋነኛ ማሳያና ስኬታማ አጋር ሆና የቀረበች ሲሆን፤ የኤምሬቶች-አፍሪካ ግንኙነት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ መካከል አዲስ እና ተራማጅ የ“ደቡብ-ደቡብ” (South-South) የትብብር ሞዴል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በአዝመራው ሞሴ