Search

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአገልግሎት አሰጣጥን ሙሉ በሙሉ የሚቀይረው 6ኛው የታርጫ መሶብ አንድ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 71

የታርጫ መሶብ አንድ ማዕከልን መርቀው የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ መንግሥት ከዜጎች ለሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

እስካሁን ባሉት በስድስቱም ማዕከላት ከ130 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማስተሳሰር የተቻለ ሲሆን፣ ማዕከሉ የአገልግሎት አሰጣጥን ከማቀላጠፍ ባሻገር የመረጃ አያያዝ እና የአደረጃጀት ሥርዓትን ወጥ እንደሚያደርገው ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊ ገበየሁ በበኩላቸው፣ የማዕከሉ ሥራ መጀመር ዜጎች በአንድ ጣሪያ ሥር በርካታ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ትልቅ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ማድረግ መቻሉ ነባራዊ የሥራ ባህላችንን እንድናሻሽል ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ በዞኑ በሚገኙ 3 የከተማ አስተዳደር መዋቅሮችም ተመሳሳይ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኢቢሲ ያነጋገራቸው የታርጫ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የአገልግሎቱ መጀመር በተለያዩ ጊዜያት ለተጠየቀው ጥያቄ የተሰጠ ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ሌሎች የልማት ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በሰለሞን ባረና