Search

በአፍሪካ እና በቻይና መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሄደ

ዓርብ ግንቦት 28, 2018 64

የአፍሪካ ህብረትና ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በአፍሪካ ህብረት የቻይና ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ጂያንግ ፌንግን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሊቀመንበሩና አምባሳደሩ በውይይታቸው በአፍሪካ ህብረት እና በቻይና መካከል ባለው ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዲሁም የጋራ ፍላጎት በሆኑ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በውይይቱ ወቅት በቻይና-አፍሪካ ትብብር መድረክ (FOCAC) ስር የሚከናወኑ ተግባራትን ጨምሮ በአህጉሪቱና በቻይና መካከል ያለው ዘላቂ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

በተጨማሪም ቻይና አፍሪካ ቅድሚያ ለምትሰጣቸው የልማት ጉዳዮች የምታደርገውን ድጋፍ እና አዳዲስ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችም ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።

ሁለቱ ወገኖች ለሉዓላዊነት፣ ለግዛት አንድነት እና ለባለብዙ ወገን ትብብር መርሆዎች ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት መግለፃቸውን የዘገው ኢዜአ ነው።

የአህጉሪቱን ሰላም፣ ልማትና የጋራ ብልጽግና ለማረጋገጥም ይበልጥ ጠንካራ የአፍሪካ ህብረትቻይና አጋርነት መፍጠር እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውም ተገልጿል።