የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አገራዊ አንድነትን፣ አብሮነትንና ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የአማራ ክልልን የ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በባሕር ዳር ከተማ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል፡፡
አቶ አረጋ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የመረዳዳት ባህልን በማጎልበት ለዜጎች ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን እያስገኘ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዘንድሮው የክረምት ወቅትም በክልሉ በተለያዩ የስራ ዘርፎች በርካታ የዜጎች በጎ ፈቃድ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ልማትን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረውና በአሁኑ ወቅት ባህል እየሆነ የመጣው የማዕድ ማጋራት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የማህበረሰባችን የቆየ እሴት የሆነው የእርስ በርስ የመረዳዳትና የመጠያየቅ ባህል ይበልጥ እንዲጎለብት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ ሕዝብም ይህንን በጎ ተግባር ወደ መሬት ለማውረድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የክረምት ስምሪት በ17 ዋና ዋና የስራ ዘርፎች ላይ ከ9.8 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኛ ዜጎችን በማሳተፍ፣ ከ15 ሚሊዮን በላይ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
በተስፋሁን ደስታ