የትምህርት ሚኒስቴር በባሕር ዳር ከተማ በ1.4 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚያስገነባውን ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዛሬው ዕለት ግንባታውን አስጀምረዋል።
በዚሁ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ የትምህርት ዘርፉን ስብራት ለመጠገን ሚኒስቴሩ አሠራርና ፖሊሲዎችን በመቀረጽ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ባለፉት 40 ዓመታት ለትምህርት ፖሊሲው የተሰጠው ትኩረት ደካማ መሆኑ፣ የጥራት ውስንነት እና የፍትሐዊ ተደራሽነት ማነስ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ውድቀት አስከትሎ መቆየቱንም ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ባለፉት የለውጡ ዓመታት በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በመቅረፍ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሀገሩን የሚወድ ትውልድ ለማፍራት ሁሉን አቀፍ ግብዓት የተሟላላቸው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች እየተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ያስጀመሩት ይህ ግንባታም የመንግሥት የትምህርት ትኩረት ማሳያ ሲሆን፣ ሥራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፤ ትምህርት ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፣ የክልሉ መንግሥት ዘርፉን በ25 ዓመት አሻጋሪ ዕቅድ ውስጥ በማካተት በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በክልሉ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ፣ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዙ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን የማፍራት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
በተስፋሁን ደስታ
#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: