Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች

ሰኞ መስከረም 25, 2019 210

✍ የኢትዮጵያ ሕዝብ በበርካታ ውዥንብሮች እና የጸጥታ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ በምርጫው ላሳየው ተሳትፎ በማመስገን፤ ይህ ሂደት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል መሠረት እየጠነከረ መምጣቱን አረጋግጧል ብለዋል።

✍ ዓለም ፈጣን፣ ያልተጠበቀ እና መተንበይ በማይቻል የጂኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ለውጥ ውስጥ መሆኗን ጠቁመዋል።

✍ ኢትዮጵያ ባለፈው ታሪኳ ከኢንዱስትሪ አብዮቶችም ሆነ ከውጭ ወረራዎች አኳያ በነበራት አለመዘጋጀት የከፈለችውን ዋጋ በማስታወስ፣ አሁን ላይ ለሚመጣው የዓለም ለውጥ በንቃት መዘጋጀት እንዳለባት አሳስበዋል።

✍ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ መገናኛ ላይ እንዲሁም በዓለም የነዳጅ መተላለፊያ አቅራቢያ መገኘታቸው ልዩ ዕድልም ፈተናም መሆኑን ጠቅሰው፣ አቅም ገንብተን ጠንክረን ከተገኘን የራሳችንን ዕድል ራሳችን እንደምንወስን፣ ከደከምን ግን ሌሎች እንደሚወስኑብን አብራርተዋል።

✍ የሀገራችንን የዘመናት ቁጭት ወደ ሥልጣኔ ለመቀየር መፍትሔው የውጭ አስተሳሰቦችን እንዳለ መገልበጥ ሳይሆን፣ ነባር እና ሀገር በቀል እሴቶችን ከውጭው ጠቃሚ ዕውቀት ጋር በማዋሃድ በመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ መገንባት መሆኑን አስምረውበታል።

✍ ባለፉት ዓመታት ከተናጠል ዘርፍ ወደ ብዙኃ ዘርፍ በመሸጋገር በተተገበሩ ሪፎርሞች በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በኮሪደር እና የቱሪዝም ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ እንዲሁም የልማት ድርጅቶችን ከኪሳራ በማውጣት በኩል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ዘርዝረዋል።

✍ ሀገራችን የገጠሟትን የኮቪድ-19 ጫና፣ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ መገለል እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የተደረጉ ሙከራዎችን በጽናት መሻገሯን በማንሣት የኢትዮጵያን አይበገሬነት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

✍ መንግሥት በቀጣይ የሥራ ዘመኑ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ግኝቶች ላይ ተመሥርቶ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ እንደሚያደርግ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሠራ፣ እንዲሁም የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከግብ እንደሚያደርስ ቃል ገብተዋል።

✍ ሙስናን፣ ሌብነትን እና አድሎአዊ አሠራሮችን ለማስወገድ መንግሥት ጥብቅ እርምጃዎችን እንደሚወስድ፣ የሲቪል ሰርቪስ አሰጣጥን እንደሚያዘምን እና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በትውልድ ግንባታ ላይ አበክሮ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

✍ የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተ የ"ሰጥቶ መቀበል" መርህ ለማሳካት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

✍ በቀጣናው የአየር የበላይነትን ጨምሮ ሀገራችንን ከማንኛውም ጥቃት አስቀድሞ መከላከል እና ማሸነፍ የሚችል ዘመናዊ፣ ፈጣሪ እና ዝግጁ የሆነ የመከላከያ እና የደኅንነት ኃይል እንደሚገነባ አብራርተዋል።

✍ በጫካ ያሉ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለብሔራዊ ጥቅም እንዲቆሙ፣ ወጣቶች እና አረጋውያን በዕውቀት እና በሥነ-ምግባር የሀገር ግንባታ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

✍ አዲሱ ፓርላማም የመንግሥትን ሥራዎች በቅርበት እንዲከታተል እና እንዲመራ አደራ ብለዋል።

በለሚ ታደሰ

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: