Search

4ኛው የፓን-አፍሪካ የቀዶ ሕክምና ጤና አጠባበቅ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

ሓሙስ ኅዳር 10, 2019 87

በአፍሪካ ሀገራት የቀዶ ሕክምና እና የሰመመን አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የጋራ መለኪያዎችን ለማጽደቅና የመረጃ ሥርዓቶችን ለማጠናከር ያለመው 4ኛው የፓን-አፍሪካ የቀዶ ሕክምና ጤና አጠባበቅ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

"የአፍሪካን የቀዶ ሕክምና መረጃ እና አመልካቾች መዋቅር መገንባት" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው የፎረሙ የመክፈቻ ንግግር ላይ፣ አስተማማኝ መረጃ ለበጀት ድልድል፣ ለተጠያቂነት እና ለጥራት መሻሻል ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።

የመረጃ ግንባታ ሂደቱ አነስተኛ እና ጠቃሚ አመልካቾችን በመምረጥ፣ ነባር የመረጃ ሥርዓቶችን በማጠናከር፣ ፍትሐዊነትንና ጥራትን በማረጋገጥ እንዲሁም መረጃን የሕዝብ ሀብት በማድረግ መመራት እንዳለበት ተጠቁሟል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት በተገበረቻቸው የቀዶ ሕክምና ዕቅዶች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች እና ያሉባት ክፍተቶች ቀርበዋል።

በዚህም የተመረጡ የቀዶ ሕክምና ተቋማት በ94 በመቶ ወረዳዎች መድረሳቸው፣ መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ድርሻ ከ44 በመቶ ወደ 78 በመቶ ማደጉ እና የሰው ኃይል ጥምርታ ከ0.35 ወደ 5.9 መሻሻሉ ተመልክቷል።

በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ድኤታው ዶ/ር ሙሉቀን አርጋው፣ ታካሚዎች በሕክምና ወጪ ምክንያት የሚደርስባቸውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በፈረንጆቹ 2030 በ30 በመቶ ለመቀነስ መታቀዱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ቀጣይነት ያለውና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት የሚሰጡት 82 በመቶው ተቋማት ብቻ መሆናቸው፣ የባለሙያ እጥረት መኖሩ እና ከቀዶ ሕክምና ጋር የተያያዘ የሞት መረጃ ልዩነት መታየቱ እንደ ክፍተት ተመላክቷል።

እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላትና መረጃን ማዕከል ያደረጉ ግቦችን ለማሳካት ከ2026 እስከ 2030 ሀገራዊ የቀዶ ሕክምና መዝገብ ለማቋቋም፣ የክሊኒካል ኦዲት ትስስርን ለማጠናከር እንዲሁም የግል የጤና ተቋማት ሪፖርት እንዲያደርጉ ለማስገደድ መታቀዱ ተገልጿል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይም አባል ሀገራት ተግባራዊ የጋራ አመልካቾች ላይ እንዲስማሙ፣ የኢንቨስትመንት አዋጭነት ማስረጃ እንዲያቀርቡ እና ሊተገበሩ የሚችሉ ቃል ኪዳኖችን ይዘው እንዲወጡ በኢትዮጵያ በኩል ጥሪ ቀርቧል።

በሳራ ሳህለሥላሴ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: