ኢትዮጵያ የአፍሪካን የንግድ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ቁልፍ የሆኑ የጥራት መሠረተ ልማቶችን እያጠናከረች መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን የአፍሪካ ንግድ ልማት ፎረም 2026 በይፋ አስጀምረዋል።
በዚህ ወቀት እንደተናገሩት አፍሪካ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይል እና እያደገ የመጣ ገበያ ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ለመቀየር ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወደ ተጠናቀቀ ምርት አቅራቢነት መሸጋገር ይገባታል።
ለዚህም እሴት መጨመር የኢንዱስትሪ አቅምን ማሳደግ እና ከተበታተኑ ገበያዎች ወደ አንድ የተሳሰረ አህጉራዊ ገበያ መምጣት ወሳኝ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በመደመር መንግሥት የጥራት መሠረተ ልማትን ለማጠናከር ደረጃዎችን፣ ምርመራን እና ቁጥጥርን የሚያካትቱ ተቋማት በአንድ የተቀናጀ ሥርዓት መደራጀታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ምርቶች የዓለምን የጥራት መስፈርት እንዲያሟሉ እና በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማገዙም ባሻገር፣ ሸማቾችን ደረጃቸውን ካልጠበቁ ምርቶች እንደሚጠብቅ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ የመንገድ፣ የባቡር፣ የኃይል እና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት እና ቀጣናዊ ገበያዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የተጀመረው ሂደትም የንግድ ሥርዓቱን የበለጠ ተገማች እና ተዓማኒ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ፣ በክህሎት እና በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የንግድ ሎጂስቲክስን ማሻሻል እንዲሁም በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ፣ በባንኮች እና በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር የአፍሪካን የንግድ አቅም ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን አህጉራዊ ሽግግር በተግባር ለመምራት ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ ንግድ ልማት ፎረም በጥራት የተደገፈ የአፍሪካ ወጪ ንግድን ለማሳደግ እና የአህጉሪቱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማጠናከር ያለመ ነው።
በአሸናፊ እንዳለ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: