ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚስተናገዱበት 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። ጉባኤው አፍሪካ የጤና ሥርዓቷን በራሷ ለመምራትና ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።
የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት አህጉሪቱ በውጭ እርዳታና አቅርቦት ላይ ያላትን ጥገኝነት በመቀነስ ወደ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የማምረት እና ፈተናዎችን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ የምታደርገውን ሽግግር ያመላክታል።
ይህም ለድንገተኛ የጤና አደጋዎች ያለውን ተጋላጭነት በመቀነስ ወደ ባለቤትነት እና የመቋቋም አቅም የሚደረግ ወሳኝ ለውጥ ነው።
በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤው የፖለቲካ መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የፈጠራ ባለሙያዎችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አካላትን እና ወጣቶችን አሳትፏል።
የጉባኤው ዋና ዓላማም አፍሪካ አደጋን የመቋቋም አቅም ያለው ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የምትከተለውን አቅጣጫ መወሰን እና የውጭ እርዳታ ጥገኝነትን ለመቀነስ ነው ተብሏል።
ጉባኤው የጤና ፋይናንስ አቅርቦትን ለማሻሻል እንዲሁም የአህጉሪቱ የጤና ደኅንነት በአፍሪካውያን አመራር፣ ፈጠራ እና አጋርነት እንዲመራ ለማስቻል ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል አዲስ አበባ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ ብቃቷና ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷ እያደገ መጥቷል።
ከተማዋ በኮሪደር ልማቱ ውብና ጽዱ ሆና የተዘጋጀች ሲሆን፣ የንግዱ ማኅበረሰብም ከጉባኤው ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች ኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት ወግና ባህልን ጠብቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: