የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር አመራር እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን የመቐለ መሶብ አገልግሎት ማዕከልን ለመክፈት የሚያስችል ዝግጅት በፌደራል መሶብ ስልጠናና ልምድ እየወሰደ ይገኛል።
በመቐለ ከተማ ለመክፈት ለታቀደው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ናቸው።
በዚህ ሂደት ከትግራይ የሄዱ የአመራር እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በአዲስ አበባ በሚገኘው የፌደራል መሶብ አገልግሎት ማዕከል ስልጠናና ልምድ እየወሰዱ መሆናቸው ተገልጿል።
የመሶብ አገልግሎት ማዕከል የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች በአንድ ቦታ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሕዝብ የሚቀርቡበት ሥርዓት ሲሆን፣ ተገልጋዮች ከአንድ መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ ሳይዘዋወሩ፣ በረጅም ወረፋ ሳይቆዩና ብዙ ወረቀቶች ሳይጠየቁ በፍጥነትና በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።
በአገልግሎት ማዕከሉ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት (ፋይዳ)፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ኢትዮ ፖስታ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም ይገኙበታል።
ሥርዓቱም ከፌደራል ደረጃ አልፎ በተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች እየተስፋፋ ይገኛል።
በመቐለ ለመክፈት ታቅዶ ያለው የመሶብ ማዕከል፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ይበልጥ በፍጥነት፣ በቀላሉ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሕዝብ ለማቅረብ የሚያግዝ ተስፋ ሰጭ እድገት ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: