አፍሪካ በጤና ዘርፍ የራሷን ፍላጎት የምትወስን፣ መፍትሔዎቿን የምታመነጭ እና ለዜጎቿ የሚደርስ ዘላቂ አገልግሎት የምታረጋግጥበት አዲስ የትብብር መድረክ የፈጠረው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ሕዝብ ጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ኅዳር 18 ቀን 2019 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ ታላቅ ጉባኤ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የተጠበቀ ሲሆን፣ መድረኩ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) በጋራ ተዘጋጅቷል።
በጉባኤው ላይ የሀገራት መሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም በፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት በመሳተፍ የአህጉሪቱን የጤና ዕጣ ፈንታ የሚመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮችን በስፋት ይመክራሉ።
ጉባኤው "የአፍሪካ የጤና ደኅንነትና ሉዓላዊነት ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ሲሆን፣ መሪ ሐሳቡ አህጉሪቱ የራሷን የጤና ፖሊሲ፣ የሳይንስ አቅም እና የምርት አቅም በማጠናከር በራስ የመተማመንና የባለቤትነት ስሜትን ለማጎልበት ያላትን ቁርጠኝነትና ፍላጎት በግልጽ ያመለክታል።
በአምስት ቀናት ቆይታ ውስጥ የመድኃኒት እና ክትባት ምርትን ማስፋፋት የጤና ፋይናንስ አማራጮች ዲጂታል ጤናና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም የወረርሽኝ ዝግጁነት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በጤና ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ዋነኛ የውይይት አጀንዳዎች ናቸው።
ጉባኤው አፍሪካ በጤና ዘርፍ ዘላቂ ራስን መቻልን እና በራስ የመወሰን እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የምትጠቀምበት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነም ተመላክቷል።
በሙሉ ግርማይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: